መግቢያ
የዚህች መጽሐፍ መነሻ በ2017 ሜይ ወር የጻፍኩትና በዕዝራ የኢንተርኔት መጽሔት የበተንኩት፥ 'ሰው መንፈስ ነው? ወይስ ሰው ነው?' የሚል መጣጥፍ ነው። ያንን ጽሑፍ የጻፍኩት በጊዜው ይህ ትምህርት እየተነዛ ነበርና፥ ከበርካታ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቄ፥ አንድ የተጻፈ ነገር በእጃቸው እንዲኖራቸው በማሰብ ነው። የመጀመሪያውን ጽሑፍ ከጻፍኩ በኋላም በርካታ ጥያቄዎች በየጊዜው እየተጠየቅሁ አጫጭር ምላሾች ስሰጥ ቆይቻለሁ፡፡
የመጀመሪያው ጽሑፍ ተደራሾች ጥቂት ሺህ ሰዎች ብቻ ስለነበሩ፥ በማኅበራዊ ገጾች ማካፈል አስፈላጊ ስለመሰለኝ በቪድዮ በሰባት ተከታታይ ክፍሎች አዘጋጅቼ አቀረብኩት። ... ለቪድዮ ትምህርት ማስታወሻ ጽሑፎች ሳዘጋጅ ቀድሞ በነበረው ጽሑፍ በብዙ ጨምሬበት ስለነበረ፥ ደግሞም በየጊዜ የመለስኳቸው ጥያቄዎችም እየተጨመሩበት ያ የመጀመሪያው መጣጥፍ ስለዳበረ በመጽሐፍ መልክ ቢቀርብ ሌሎችን ሊጠቅም እንደሚችል በማመን በዚህ መልኩ እንደገና ቀርቧል።
አንዳንድ ጥያቄዎች መልሳቸው ገሐድ ስለሆነ ሞኝ ጥያቄዎች ይመስላሉ። 'ሰው ሰው ነው? ወይስ መንፈስ ነው? ሰው ሰው ነው? ወይስ ሰው ወይስ እግዜር ነው?' ብሎ መጠየቅ ጅልነት ይመስላል። ምክንያቱም፥ ነገሩ ገሐድ ነዋ! ይሁን እንጂ፥ ጥያቄው እንዲጠየቅ ግድ የሚያደርጉ ነገሮች ሲፈጠሩ፥ ሰው ሰው አይደለም የሚሉ ስሕተቶች ሲናኙ፥ 'ሰው መንፈስ ነው፤ ሰው እግዜር ነው፤ እኔና አብ አንድ ነን፤ እኔ የእግዚአብሔር ዓይነት ነኝ፤' የሚሉ ስሕተቶች ሲነገሩ፥ እውነት እየመሰሉ ሲመጡ፥ ያኔ ሞኝ ጥያቄ መጠየቅ ግድ ይሆናል። 'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' ሲባል መስማት በወንጌላውያን አማኞች አካባቢ አዲስ አይደለም፡፡
ይህ የዘመናዊዎቹ የስሕተት ትምህርቶች ሁሉ እናት በሆነችው በአሜሪካ ውስጥ የተወለደ፥ እዚያው አሜሪካ ጡጦ ጠብቶ ያደገና በዓለም ዙሪያ የተወነጨፈ፥ ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች በማደጎ የራሳቸው ልጅ ያደረጉት፥ በእውቀትም፥ ያለ እውቀትም፥ በስሕተትም፥ በመታለልም፥ የተቀበሉት፥ ያሳደጉት የስሕተት ትምህርት ነው። ይህ 'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' የሚባለው ነገር የቃለ እምነት ስሕተት የተጣረሰ ስነ ሰብእ ነው።
እንደዚህ ያለ አሳችና አሳሳች ነገር በመኖሩ፥ 'ሰው ምንድርን ነው?' ተብሎ መጥጠየቅ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊው የሰው ማንነት ትምህርት መገለጥ አለበት፡፡ በአገራችን ይህንን ስሕተት ከመንዛት ጋር የሚቆራኙ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም ምንጩ ግን እነርሱ አይደሉም። ከማን ተኮረጀ? ከየት መነጨ? ያንንም እንመለከተዋለን፡፡