አራት፤ መከራ በእግዚአብሔር እይታና ተካፋይነት
የሰውን ውድቀት ተከትሎ የኃጢአት መዘዝ የሆነው የተፈጥሮ መዛባት፥ የሰው ጭንቅና ስቃይ፥ በሌላው ላይ መክፋት ተከተለ። መከራና ሞት የውድቀት መዘዞች ናቸው እንጂ ሰማይና ምድር፥ ፍጥረታትና ሰው ሲፈጠሩ አብረው የተፈጠሩ ነገሮች አይደሉም። ሰው ከዔድን ገነት ከመውጣቱ በፊት ፍርድ ተበየነ፤ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከወጣ በኋላም ብልሽቱ ቀጠለ። የኃጢአት እና የመዘዞቹ መኖር እግዚአብሔርን ተጠያቂ አያደርገውም። አንድ ነገር እንዳይሆን አላደረገም ወይም አልከለከለም ማለት እግዚአብሔር በዚያ ነገር መሆን ወይም መፈጸም ተስማምቷል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሉዓላዊ አምላክ ቢሆንም በሰዎች ፈቃድ ላይ ግዴታን አይጭንም።
እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዳይሆን አላደረገም ማለት በዚያ ነገር ተስማምቷል ወይም ፈቅዷል ማለት አይደለም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፥ ወደ ቅዱሳኑ የሚመጣ ማናቸውም ነገር ያለ እርሱ ፈቃድና እርሱ ሳያውቅ ይመጣል ማለትም አይደለም። አንዳንድ መከራዎችና ፈተናዎች በራሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ እና በራሱ በእግዚአብሔርም ወደ ቅዱሳን ይመጣሉ፡፡ እንዲህ ከሆነ እነዚህ ፈተናዎችና መከራዎች ሥራና ግብ አላቸው ማለት ነው። ይህ እውነት ቅዱሳንን ግር ሊያሰኝ ይቻል እንጂ ግን እውነት ነው፡፡
ሁላችንም ከልባችን ስር የምናውቀው እውነትና የማንክደው ሐቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት የሚልቀውና የሚጠነክረው በድሎትና በቅንጦት ስንሆን ሳይሆን በፈተናና በመከራ ውስጥ ስናልፍ ነው፡፡ ያ ጊዜ የምንጾምበትና የምንጸልይበት፥ እርሱን ለመምሰል የምንጥርበትና በተወልን ምሳሌነት የምንሄድበት ጊዜ ነው። መንፈሳዊ ማንነታችን ተፈልቅቆ ይወጣል። ምንም ይሁን፥ ምንም ይምጣ፥ ከፊቱ ላንጠፋ፥ ከቤቱ ላንወጣ የምንምልበት ጊዜ ነው፡፡
ኢዮብ ቀድሞም መንፈሳዊ ሰው ነው። የደረሰበት ለምን እንደሆነ ሳይገባውም፥ "ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ። እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ፡፡" አለ፤ ኢዮ 13፥14-15። ይህ ሰው ሲጨልምበት እየደመቀ መጣ። "እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤" ያለው ሰው፥ የትዕግሥት ምሳሌም ሆነ፤ ያዕ. 5፥11። በምንም የሰው መለኪያ ብንሰፍረው እኮ ኢዮብ የሆነበት ሁሉ ሊሆንበት የተገባው ሰው አይደለም፡፡ ደግነቱ መለኪያችን የሰው መለኪያ ብቻ ነው፤ የወደቀ ሰው መለኪያ።
በዮሐ. 15፥2 እንደተጻፈው፥ ሲያጠራን ብዙ ፍሬ እንድናፈራ ነው። ማጥራት መግረዝ ነው። ፈተና መከራና ስቃይ በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ያሉ መቅረጫ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ልጁን እንድንመስል፥ ፍለጋውን እንድንከተል የሚያደርጉን መሳሪያዎች ናቸው፡፡ "የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።" 1ጴጥ. 2፥21። ምሳሌ ትቶልን ስለ እኛ መከራ የተቀበለው፥ እኛ ስለ ሌሎች መከራ ባንቀበልም፥ ለሌሎች አርዓያ ልንሆን፥ ምሳሌውን እንድንከተል ነው።
አንዲት በስቃይ ውስጥ እያለፈች ያለችን ክርስቲያን ለመጎብኘት የሄደ መጋቢዋ ሰቆቃዋን ከሰማ በኋላ፥ እግዚአብሔርንም ለማማረር መቅረቧን ከተረዳ በኋላ፥ ሻይ ልታቀርብ ስትሰናዳ፥ የሻይ ማስቀመጫ ኩርሲ ላይ ያለውን፥ ሴቲቱ ራስዋ በእጇ የሠራችውን እጅግ የሚያምር የጥልፍ ጨርቅ ገልብጦ በኩርሲው ላይ አነጠፈውና፥ ስትመለስ፥ 'ምን ዓይነት ሴት ናት እንዲህ የመሰለ የተመሰቃቀለ፥ ትርጉም የማይሰጥ ጥልፍ የጠለፈች ሴት? ደግሞ እንደዚህ ዓይነት አስጠሊ ነገር ለመሥራት ጊዜዋና ማቃጠሏ!' አለና በመገረም ይመለከት ጀመር። ኋላ ሻያቸውን እየጠጡ ሳለ ስለ ጥልፉ አነሣና፥ 'ይህንን ጥልፍ ስትጠልፊው በየት በኩል ነበር የምታዪው? በጌጡ ወይስ በፈርሱ?' አላት። በጌጡ በኩል እያየች እንደምትጠልፍ ነገረችው። 'አንድ ሰው የምትሠሪውን ሥራ በፈርሱ በኩል ብቻ ቢያይ ምን ይል ይመስልሻል? ጠየቃት፡፡ አልመለሰችለትም፤ መመለስም አላስፈለጋትም፡፡ 'አየሽ እግዚአብሔር ጌጥ ሲሠራ ለማየት ከእርሱ በኩል ሆነሽ ነው ማየት ያለብሽ።' አላት፡፡
"እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።" ሮሜ 8፥28። ነገር ሁሉ የሚለው ውስጥ መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ መልካም ያልሆኑ መከራዎችም መኖራቸው ይታወቃል። ነገሮቹ መልካም ባይሆኑም ለበጎ የመሆናቸው ምስጢር የሚገኘው በቀጣዩ ጥቅስ ነው። "ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤" ቁጥር 29። በቅዱሳን የሚሆኑ ማናቸውም ነገሮች ግባቸው የእኛን ክርስቶስን ለመምሰል መቅረጽ ነው፡፡
ይህንን ለማድረግ የገዛ ልጁን ሳይራራ በመስጠት ፈጽሞታል፡፡ "ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?" ቁ. 32። መከራና ስቃይን ስናስብ እግዚአብሔር ራሱን ከመከራ ከልሎና ሸሽጎ ሰውን ብቻ የመከራ ገፈት ጠጪ ያደረገ ከመሰለን ተሳስተናል። እግዚአብሔር በሰው ከፋትና ስቃይ የተነሣ ሰውን በመፍጠሩ እስኪጸጸት ድረስ ነው ያዘነው። 'ተጸጸተ' የሚለው ቃል አቃሰተ፥ እህህ አለ፤ ማለት ነው። እንጂማ ሰው ተሳስቶ እንደሚጸጸት ያለውን ጸጸት እግዚአብሔር አይጸጸትም፤ እርሱ አይሳሳትምና፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ የሰውን፥ የሰውነትን፥ ሰው የመሆንን መከራና ስቃይ ተካፍሏል። ሰው ሲሆን ለራሱ የተለየ ሥጋ አላዘጋጀም፤ መከራውንም አላቀለለም፡፡ ኃጢአትን አላደረገም እንጂ በሁሉ ተፈተነ፤ ስቃይንም ተቀበለ። ጌታ ሰው ሲሆን፥ በሥጋ ሲመጣ፥ ለራሱ ሌላ ሕግ አልደነገገም። በሕጉ፥ በወጉ መሠረት ነው እሜዳው ውስጥ የተጫወተው። ሰው ሲሆን የመከራን መንገድ እስከ ጥግ ተጉዞታል፡፡ ድህነትን ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ያውቃል፤ በበረት ውስጥ ነው የተወለደው፤ ሉቃ. 2። ሲወለድ ብቻ አይደለም፤ ሲኖር ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ አልነበረውም፤ ማቴ. 8፥20። ሲኖር ብቻ አይደለም፤ ሲሞትም የተቀበረበት መቃብር የተውሶ ነበረ፤ ማቴ. 27፥60። ለነገሩ፥ ለ3 ቀን ቆይታ የግዢ መቃብር ይበዛል። ጌታ እጦትን የሚያውቅ ነበር፤ እጦትን ብቻ ሳይሆን "የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤" ኢሳ. 53፥3። ጕስቍልናን ያውቃታል፤ ለስቃይ እንግዳ አይደለም፡፡ ለምንፈተንበት ፈተናና ለምናልፍበት እንግልትና መከራ ባይተዋር አይደለም።
እኛ ባለፍንበት ጎዳና እርሱ ሄዶ፥ እርሱ ባለፈበት ጎዳና መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው ጋበዘን፤ ማቴ. 16፥24-25፤ ሉቃ. 9፥23-24። ይህ ጎዳናና ይህ መከተል ሐዋርያቱም፥ ደቀ መዛሙርቱም፥ የቀደሙት ቅዱሳንና አብያተ ክርስቲያንም ያለፉበት ጎዳና፥ ያስተማሩትም ትምህርት ነው፤ ሮሜ. 5፥3፤ ያዕ. 1፥2-4። መከራ የመንፈሳዊ ሕይወት ማላቂያና የእምነት ማንጠሪያ እሳት ነው፤ 1ጴጥ. 1፥7-8። ክርስቶስ የመከራ ምሳሌያችን ነው፤ "የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።" ዕብ. 12፥1-2። "በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤" 1ጴጥ. 2፥19-23።
ፍለጋውን እንድንከተል ክርስቶስ ስለ እኛ መከራን ተቀብሎ የተወልን ምሳሌን ነው። ይህ ምሳሌ የተባለው ቃል፥ ሁፖግራሞስ በላዩ የሚጻፍበት ካርቦን ኮፒ እንደማለት ነው። በላዩ የሚኬድበት የተቀደደ ፈር፥ ንድፍ ወይም ትልም ነው።