የህይወት ቃል ህብረት Logo

የይሁዳ መልእክት

አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት መጋደል

በ ዘላለም መንግሥቱ

መግቢያ

ይህ ዘመን ከመቼውም ይልቅ ሐሰተኛ ነቢያት የበዙበት ነው፡፡ ሐሰተኛ ነቢያትና የሐሰት አስተማሪዎች የሐሰት አባት ሰይጣን በዔድን ገነት ሔዋንን ካሳተባት ጊዜ ጀምሮ ነበሩ፡፡ እስከ ፍጻሜ ዘመናትም ይቀጥላሉ፡፡ በብሉይ ኪዳንም ነበሩ፤ በጌታ ዘመንም ነበሩ፤ በሐዋርያቱም ዘመን ነበሩ፡፡ ዛሬም በእኛ ዘመን በዝተው ይገኛሉ፡፡

ይሁዳ መልእክቱን በጻፈበት ዘመን ሐሰተኞች አሳሳቢ ሆነው ነበር። ይህ ችግር ይሁዳን የመልእክቱን ይዘት እስከማስቀየር ያደረሰው አሳሳቢነት ጉዳይ ነበረ። ስለዚህ ነው በቁጥር 3 ላይ፥ "ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡" ያለው፡፡

ዛሬም የሐሰተኛ ነቢያት ጉዳይና ብዛት አሳሳቢ ነው። ቅዱስ ቃሉ የሚያስተምረንም በመጨረሻው ዘመን ይህ አሳሳቢነት እንደሚቀንስ ሳይሆን እንደሚጨምር ነው። ጌታ ይህን አስተምሮአል። በማቴ. 7፥22 "በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።" ብሎአለ። በማቴ. 24፥5 እና 11 "ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤" ብሎአል። ሐዋርያው ዮሐንስም ከማሳሰቢያ ጋር፥ "ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን፡፡" "ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።" ብሎአል፤ 1ዮሐ. 2፥18 እና 4፥1።

ይሁዳ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሲጽፍ ይህን አስተውሎአል፡፡ በጣም በግልጽ ቋንቋና በብዙ ምስላዊ ምሳሌዎችም አድምቆ ነው የጻፈው። ማስጠንቀቁ በእጅጉ አስፈላጊ ነበር። በዚህች አጭር ለግል ንባብም ለቡድን ጥናትም የተዘጋጀች ሐቲት ይህንን የይሁዳን አሳሳቢና አስጠንቃቂ አሳብ እንካፈል፡፡

የይሁዳ መልእክት (ሙሉ ምዕራፍ)

1፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤

2፥ ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ፡፡

3፥ ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።

4፥ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ፡፡

5፥ ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡

6፥ መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።

7፥ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።

8፥ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፡፡

9፥ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡

10፥ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።

11፥ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል፡፡

12፥ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥

13፥ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።

14-15፥ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ፡፡

16: እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል፡፡

17፥ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤

18፥ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።

19፥ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

20፥ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥

21፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።

22፥ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥

23፥ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።

24፥ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው፥

25፥ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

ማን ጻፈው? ለማን ጻፈው? ለምን ጻፈው?

ማን ጻፈው?

ማን ጻፈው? በግልጽ እንደተጻፈው የይሁዳን መልእክት የጻፈው ይሁዳ ነው፡፡ 'የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥' ይላል። ይህ ይሁዳ የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ መሆኑን ነው የጻፈው። በዘመኑ የእገሌ ልጅ እገሌ እንጂ የእገሌ ወንድም እገሌ ብሎ መልእክት መጻፍ የተለመደ አይደለም፡፡

ያዕቆብ ራሱ ማን መሆኑን መመልከት ተገቢ ነው። ይህ ያዕቆብ የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ አይደለም። የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ ቤተ ክርስቲያን ገና ጨቅላ ሳለች ሔሮድስ በሰይፍ አስገድሎታል፤ ሐዋ. 12፥1-2። ይህ ያዕቆብ የያዕቆብን መልእክት የጻፈው በኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን የታወቀው መሪ ነው። ይህ ያዕቆብ ከጌታ ወንድሞች አንዱ ነው። ከትንሣኤው በኋላ በጌታ ያመነና በመልእክቱ ውስጥ ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ብሎ የጠራ ሰው ነው ያዕ. 1፥1፡፡

በገላ. 1፥18-19 ሐዋርያው ጳውሎስ በዓመታት በኋላ ከደማስቆ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ስላገኛቸው ሰዎች ሲናገር፥ “ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም።" አለ። ከሐዋ. 15፥13 ጀምሮ እንደምናየው ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ሽማግሌ ነው፡፡

የጌታ ወንድሞች እየተባሉ በስም ስለተጠቀሱት፥ ማቴ. 13፥55 እንዲህ ይላል። “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?" ያዕቆብ ከጌታ ወንድሞች አንዱ ነው። በማር. 6፥3ም ይኸው ተጽፎአል፡፡ ... እነዚህ ወንድሞች ከጌታ በኋላ ከማርያም የተወለዱ የዮሴፍ ልጆች እና የጌታ ግማሽ ወንድሞች ናቸው። ይህ ይሁዳ የያዕቆብ ወንድም ነው፤ የጌታም ወንድም ነው። ሆኖም፥ ያዕቆብም፥ ይሁዳ ራሱም ራሳቸውን የጌታ ወንድም ሳይሆን የጌታ ባሪያ ብለው ነው የጻፉት በእርግጥም የጌታ ባሪያም ናቸው፤ ጌታ በእውነት ጌታ ነውና።

ለማን ጻፈው?

"1፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ 2፥ ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ፡፡"

ይህኛው፥ 'ለማን ጻፈው?' የሚለው ጥያቄ፥ 'ማን ጻፈው?' እንደሚለው አወዛጋቢ አይደለም፡፡ ... 'በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤' በአብ የተወደዱ፥ ለኢየሱስ የተጠበቁ፥ የተጠሩ። የይሁዳ መልእክት ለአንድ አጥቢያ የተጻፈ ሳይሆን የተወደዱ፥ የተጠበቁ፥ የተጠሩ የሚሉት ቃላት በጥቅል ለአማኞች የተጻፈ መሆኑን ያሳያል። ... እኛም በአብ የተወደድን ነን። ዮሐ. 3፥16 ይህንን የአብን ፍቅር በግሩም ይገልጠዋል።

እነዚህ ሰዎች የተወደዱ ብቻ ሳይሆኑ ተጠብቀው የተጠሩም ናቸው። ... ክርስቲያኖች የተጠራንና ለጥሪ መልስ የሰጠን ሰዎች መሆናችንን መረዳት አለብን። ... ከተቀባዮቹ ቀጥሎ ሰላምታውን ያቀርባል። "ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ፡፡"

ለምን ጻፈው?

"3፥ ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡"

... ይሁዳ በግልጽ እንደጻፈው ሊጽፍ የጀመረው “ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን" ነው። ... ነገር ግን ... "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንዲጋደሉ እየመከረ" ይጽፍ ዘንድ ግድ ሆነበት።

ለምን? ... "4፥ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ፡፡" ... ይህን ያደረገው የስሕተት አስተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሾልከው ገብተው የእግዚአብሔርን ጸጋ በሴሰኝነት በመለወጥ አማኞችን ከእግዚአብሔር መንገድ ፈቀቅ በማድረጋቸው ምክንያት ነው።

... መጋደል ያስፈለገው ይህንን መስቀል የሚደብቁ፥ የሚሰውሩ፥ የሚለውጡ፥ የሚሸቅጡ ሐሳውያን አስተማሪዎችና ሐሰተኛ ነቢያት ገና ከመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያንን ማዋከብና ማናወጥ፥ መሸርሸርና ማፍረስ ጀምረው ስለነበረ ነው። ... ይሁዳ ሊጽፍ የተገደደው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የተጋድሎው ምክንያቶች እነማን ናቸው? (ቁ. 4)

4፥ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ፡፡

ይሁዳ እየጻፈ ያለው ስለ ሐሰተኞች ነው። ... ይሁዳ ከስማቸው ይልቅ ግብራቸውና መልካቸው ላይ ያተኮረ ማስጠንቀቂያ ነው የጻፈው፡፡

  1. ከቀድሞም ለፍርድ የተጻፉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የዳኑ አለመሆናቸውን የሚገልጥ ቃል ነው። ... ዓላማና ግባቸው በራሳቸው ለራሳቸው የተቀረጸ የሰይጣን መሳሪያዎች ናቸው፡፡
  2. ሾልከው ገብተዋል። ... እነዚህ ሰዎች ቀድሞውኑ ገብተዋል። ውስጥ ናቸው። ... ሾልከው ነው የገቡት። አደገኝነታቸውም ይህ ነው። ... ተደብቆ መጥቶ ከጎን መቀመጥ፥ መስፈር፥ መደላደል ማለት ነው። ... የሚታወቁት ጥፋትና ጉዳት ከሆነ በኋላ እጅግ ዘግይቶና ቆይቶ ነው፡፡
  3. ኃጢአተኞች ናቸው። ቃሉ መንፈሳዊነት፥ አማኝነት፥ እግዚአብሔርን መምሰል ከቶም የሊላቸው ማለት ነው። ... ጨርሶውኑ እግዚአብሔርን አለመፈለግን፥ አለመከተልን የሚያሳይ ነው፡፡
  4. ጸጋውን በሴሰኝነት ይለውጣሉ፡፡ ... ይህ ጸጋን በሴሰኝነት መለወጥ ለሥጋ የኃጢአትን ፈቃድ መስጠት ነው። ... ለሥጋ ምኞት፥ በተለይም ለብልግናና ለዝሙት አልፎ መሰጠትን የሚያመለክት ቃል ነው። ... ጸጋ መብዛቱ እውነት ነው፤ ሮሜ 5። ነገር ግን ጸጋ በዛ ብለን በኃጢአት እንድንጫወት የተፈቀደልን ሰዎች አይደለንም፤ ሮሜ 6፥1 ይህን ይነግረናል፡፡
  5. ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። "ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ፡፡" መካድ አላውቅም፤ ምንም ግንኙነትና ዝምድና የለኝም ማለት ነው። ... ይህ ክሕደት ሳያውቁ ቀርተው ተባባሪ መሆን ሳይሆን አውቆ፥ አመዛዝኖ፥ አሰላስሎ እንቢ ማለት ነው።

ማስጠንቀቂያዎች (ቁ. 5-7)

ሀ. የወደቁ እስራኤል ምሳሌነት (ቁ. 5)

5፥ ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡

ሐሰተኞችን ለመግለጥ ይሁዳ ከተጠቀመባቸው የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች አንዱ ከግብጽ የወጡና ነገር ግን፥ ወደ ተስፋዋ ምድር ያልገቡ አይሁድ ናቸው። ... "ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ" ሲል ተደራሲዎቹ ታሪኩን የተረዱ፥ ያነበቡ፥ የተማሩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

... በዘኁ. 14፥20-38 ላይ ... ከእነዚያ 603,550 ጎልማሶች ውስጥ በሕይወት ተርፈው ወደ ተስፋዋ ምድር የገቡት ሁለት ብቻ ናቸው፤ ኢያሱ እና ካሌብ። የቀሩት በሙሉ በምድረ በዳ አለቁ፤ ሞቱ፡፡ ... ያልገቡቱ ያልገቡበት ምክንያት ባለማመናቸው ጠንቅ ነው።

ይሁዳ፥ “ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡" በማለት የሚናገረው ይህንን እውነት ነው። የወጡት ሁሉ አልገቡም። ለምን? ስላላመኑ። ስላልታዘዙ፡፡ ... እነዚህ ሰዎች ድነዋል? ከግብጽ ወጥተዋል? አዎን። ግን በመንገድ ጠፉ፡፡

የይሁዳ ማስጠንቀቂያ ግልጽ ነው። መውጣት አንድ ነገር ነው። መኖር ግን ሌላ ነው። ... ሐሰተኛ ነቢያት ተከታዮቻቸውን በመንገድ አዝረክርከው የሚፈጁት ሰማያዊውን በማስጣልና ምድራዊውን በማስናፈቅ ነው። ... እንጠንቀቅ፡፡

ለ. የወደቁ መላእክት ምሳሌነት (ቁ. 6)

6፥ መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል፡፡

ቀጥሎ ይሁዳ ስለ ሐሰተኞች ምሳሌ አድርጎ ምስክር የጠራው ስፍራቸውን የለቀቁ መላእክትን ነው። ... እነዚህ መላእክት መኖሪያ ነበራቸው፤ ትተውታል፤ ... ደግሞም አለቅነት ነበራቸው፤ አልጠበቁትም፤ ... ይህ ደግሞ የሥልጣን ክስረትና ውርደት ነው፡፡

... ይሁዳ የጻፈው ከወደቁትና ስፍራቸውን ከተዉት መላእክት እዚህ የተጠቀሱት ታስረው እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚጥጠበቁ መኖራቸው ነው። እግዚአብሔር የሚቀጣ አምላክ ነው። ስፍራቸውን የተዉ መላእክት ተቀጥተዋል፤ እንደዚሁ ስፍራቸውን የተዉ ሰዎችም መቀጣታቸው የማይቀር ነው። በዚህ ጥቅስ የይሁዳ መልእክት ይህ ነው፡፡

ሌላው ማስጠንቀቂያ፥ እነዚያ መላእክት አስቀድሞ የክብር ስፍራ እና አለቅነት የነበራቸው መሆናቸው ቅጣታቸውን አላስቀረውም። ... ሐሰተኞች ነቢያት እና የሐሰት አስተማሪዎች ልክ ስፍራውን እንደተወው እንደ ሰይጣን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካዘጋጀው ዘላለማዊ ፍስሐ ራሳቸውን የጣሉ፥ ስፍራቸውን የተዉና፥ ሌሎችንም የሚያስተዉ ሰዎች ናቸው።

ሐ. የሰዶምና ገሞራ ምሳሌነት (ቁ. 7)

7፥ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል፡፡

ቀጥሎ ይሁዳ ስለ ሐሰተኞች ምሳሌ አድርጎ ምስክርና የቅጣት ምሳሌ የጠራው ሰዶምና ገሞራን ነው። ... 'እንደ እነርሱ' ሲል ... እንደራሳቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች ማለቱ ነው።

... በሕዝ. 16፥49-50 የሰዶም ኃጢአት እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ "እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው፡፡"

... ርኩሰታቸው ደግሞ በዘፍ. 19 የተጻፈው ነው። ... ይህ ሰዶማዊነት እየተባለ በኋላ የተጠራው የተመሳሳይ ጾታ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ኃጢአት ነው።

... የሰዶምና የዙሪያዋ ከተሞች ቅጣት እሳት ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ እሳትም ነው። 'በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል' ነው ይሁዳ ያለው፡፡ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ አለማወቅ ምድራዊ፥ ሥጋዊ፥ አካላዊ ቅጣት ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ ፍርድም አለበት፡፡

የከሐድያን መልክ (ቁ. 8-16)

ሀ. ተሳዳቢነት (ቁ. 8-10)

8፥ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፡።
9፥ የመላእከት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡
10፥ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ፡፡

... በእነዚህ ሦስት ጥቅሶች ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ጉልህ ቃል መሳደብ ነው። ... ሐሰተኛ ነቢያት ግን ለስድብ አፋቸው ሲከፈት ወሰን የለውም። ... ሥልጣንን መቃወምና መሳደብ የመንግሥትን ሥልጣን ሊሆን ይችላል። የቤተ ክርስቲያንንም ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የእግዚአብሔርን ነው። ... ጌትነትን መናቃቸው ጌታን መናቃቸውን ሳይሆን ሥልጣንን መናቃቸውን የሚያመለክት ነው። ጌታንማ ቀደም ሲል እንዳየነው ክደውታል፡፡

ሥልጣንን መቃወም ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ይሳደባሉ፡፡ ስድባቸው ስለማያውቁት ነገርም ነው። እውቀታቸው ደግሞ ደመነፍሳዊ ነው። በማስተዋል ሳይሆን እንደ እንስሶች በፍጥረታቸው ነው። ይህ ጎዶሎ እውቀት መጥፊያቸውም ነው።

ለ. የቃየል መንገድ (ቁ. 11)

11፥ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና...

የመጀመሪያው ምሳሌ የቃየል መንገድ ነው፡፡ ... የቃየል መንገድ የንዴትና የጥላቻ፥ የበቀልና የነፍስ ማጥፋት ነው። ... ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች የሰውን ኃጢአተኛነትና ፍጹም ውድቀት፥ የክርስቶስን ደምና መስቀሉን ከፍና ደመቅ አድርገው የማይሰብኩትና የማያሳዩት እንደ ቃየን የራሳቸውን እጅ ፍሬ ለማቅረብ ሲቃጡ ነው። ... ቃየላዊ አምልኮ የራስ መታየትና የራስ መወድስ ነው። ... ቃየላዊ አምልኮ የራስ ፍሬ መደርደሪያ ላይ የሚታይበት ነው። ... በቃየል መንገድ ሄደዋልና የተባሉት ወዮላቸው! የተባሉትና ወዮታ የተመደበባቸው ናቸው፡፡

ሐ. የበለዓም ደመወዝ (ቁ. 11)

11፥ ... ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል...

... በለዓም በገንዘብ ፍቅር የተጠመደና ገንዘብ ተቀብሎ ለመርገም እጅግ ሩቅ መንገድ ተጉዞ የመጣ ሰው መሆኑን ነው፡፡ ... በለዓም እስራኤልን እንዲረግም ባላቅ የላከበት ጥሪ ... "የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤" ... ይህ ሰው መራቂና ረጋሚ ነው። መመረቅና መርገም ሸቀጦቹ ናቸው። የሚረግመውና የሚመርቀውም በገንዘብ ነው።

... ሐሰተኛ ነቢያት የሚሠሩትን ነገር የሚሠሩት ለገንዘብ ነው። ለጥቅም ነው። ሐሰተኛ ነቢያት በፍቅረ ንዋይ የተለከፉ ናቸው። ... ሐሰተኛ ነቢያት እንደ ትንቢት፥ የውሸት ፈውስ፥ የማይፈጸም ተስፋ፥ ... እና የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ሸቀጦች በመቸርቸር ራሳቸውን እንደ ውኃ ያፈሰሱ ቃልቻዎች ናቸው።

መ. የቆሬ መቃወም (ቁ. 11)

11፥ ... በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።

ቆሬ ... በሙሴ ዘመን የነበረ ... ሌዋዊ ሰው ነው። ... ቆሬ ... የተሰጠው የከበረ አገልግሎት ስላልበቃው ያልተሰጠውን ሊወስድ ሲዘረጋ በሌላው ሳይሆን በሰጪው ላይ መነሣቱን ያላስተዋለ ሰው ነው። የቆሬና የግብረ አበሮቹ ጥፋት የሙሴንና የአሮንን ሹመት አለመቀበል ነው። የዓመጻቸው መሠረትም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሥልጣንን መቃወም ነው።

ሐሰተኛ ነቢያት እንዴት እንደሚጀምሩ ታሪካቸውን ከመሠረቱ ሄደን ስንመረምር የብዙዎቹ ጅማሬ ከቆሬና ከነአቤሮን ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሥልጣን በመቃወም እና በማመጽ ነው የሚጀመረው። ... ሐሰተኞች ነቢያትና ቆሬ በዓመጽና በተሰጣቸው ክቡር ጸጋና የአካል ድርሻ ባለመርካት፥ ዓመጸኞችን በማስከተልና በማስነሣት ይመሳሰላሉ፡፡ ጥፋታቸውና ፍጻሜያቸውም ተመሳሳይ ነው።

ሠ. እድፈኞች፣ እረኞች፣ ደመናዎች፣ ዛፎች፣ ከዋክብት (ቁ. 12-13)

12-13፥ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው፡፡

በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ውስጥ ይሁዳ የጠቀጠቃቸው የሐሰተኞች ነቢያትና አስተማሪዎች ባህርያት ብዙ ናቸው። ... ስድስት ነገሮች ተጠቅሰዋል።

  1. እድፍ ይላቸዋል። ... "በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው።" ... ሐሰተኞች በቅዱሳን ውስጥ ነውርና እድፍ ናቸው።
  2. እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ ... ራሳቸውን ይመግባሉ፥ ይጠብቃሉ፥ ያሰማራሉ ነው። ... ሐሰተኛ ነቢያት ዋና መታወቂያቸው መጋቢ ሳይሆኑ ተመጋቢ መሆናቸውና የማንም ተጠያቂ አለመሆናቸው ነው።
  3. በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ... ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ አስተማሪዎች የውሸት ተስፋ እንጂ የእውነት ጸጋ የላቸውም። ... ራሳቸውም የማይጨበጡ ናቸው።
  4. ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ ... ሐሰተኛ ነቢያት በድርቀት የተመቱ ፍሬቢስ ሰዎች ናቸው። ... የፍሬ ብቻ ሳይሆን የመኖር ተስፋም የላቸውም፡፡
  5. የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ... ነውረኞች ናቸው። ነውራቸው ደግሞ ከውስጣቸው ነው የሚወጣው። ... ሐሰተኛ ነቢያት ነውረኞች ናቸው።
  6. ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው። ... መስመር የሳተ፥ ከምሕዋሩ የወጣ አሳች የሆነ አካሄድን የሚሄዱ ... ሐሰተኛ ነቢያትም ልክ እንደዚህ ናቸው፤ መስመርና ሥርዓት የላቸውም ... ፍጻሜያቸው ድቅድቅ ጨለማ የሆነ ናቸው።

ረ. የፍርዳቸው ትንቢት፤ የሄኖክ ትንቢት (ቁ. 14-16)

14-15፥ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ ... ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።
16: እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል፡፡

ይሁዳ ... ሄኖክን ምስክር አድርጎ ይጠቅሳል። ... ሄኖክ አካሄዱን ከአምላኩ ጋር አድርጎ ቢወሰድም ኃጢአተኞችን በኃጢአታቸው እንዲቀጣ፥ እንዲፈርድ እንደሚመጣ ትንቢትን ተናግሮ እንደነበር ነው ይሁዳ የጠቀሰው፡፡ ... የይሁዳ ነጥብም ይህ የኃጢአተኞች ዓመጽና የዚህ መዘዝ የሆነው የማይቀር ፍርድ እና ቅጣታቸው ነው።

ቁ. 16 ... በመጀመሪያ እንደ ምኞታቸው የሚሄዱ ናቸው። ... ሐሰተኛ ነቢያት እና የስሕተት አስተማሪዎች ገደብ እንደሌለው የገዛ ምኞታቸው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ... ሁለት ዓይነት መልክ ያላቸው ሰዎች ናቸው። አንጎራጓሪና ስለ ዕድላቸው አጉረምራሚዎች ናቸው። ... እንዲህ ውስጣቸው የተጨራመተ ... ሆነው ደግሞ ከልክ ያለፉ፥ የተነፉ፥ ያበጡ፥ ታላላቅ ቃላት ይናገራሉ። ... ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ደግሞ "እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ" ነው። ለጥቅምና ለትርፍ ነው የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉት ማለት ነው።

ምክር ለአማኞች (ቁ. 17-23)

ሀ. ዘባቾች (ቁ. 17-19)

17፥ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
18፥ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና፡፡
19፥ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

... "እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥" ይላል። ... የተናገረው ፍሬ ነጥብም፥ "በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤" የሚል ነው። ሐሰተኞችን ለመለየትም፥ ከእነርሱ ለመጠበቅም ክርስቲያኖች ማድረግ ካለባቸው ዋና ዋና ነገሮች አንዱ አስቀድሞ ወደተሰጠው፥ ወደ ተነገረው እውነት፥ ወደ ቃሉ መመለስ ነው፡፡

... ሐዋርያት የነገሯቸው አሳቾቹ 'በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ፤ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው' ብለው ነው፡፡

... ዘባቾች ተሳላቂዎች፥ ፌዘኞችና አፊያዦች፥ ቀላጆችና ቀላማጆች፥ አቅላዮችና ሌላውን በማጣጣል መሳቂያና የተናቀ አድራጊዎች ናቸው። ... ሐሰተኛ ነቢያት ዘባችነታቸው በንቀታቸው ይታያል። እግዚአብሔርን ይንቃሉ፤ ሰዎችንም ይንቃሉ። ... "እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡" ... ሐሰተኞች ነቢያትና አስተማሪዎች ሰዎችን ወንጌል በመስበክ አይደለም ማኅበራቸውን የሚጀምሩት፤ ወንጌል የላቸውም። በመለየት፥ በመነጠል፥ በመክፈል፥ በመንፈቅ ነው የሚጀምሩት፡፡ ኑፋቄ ማለት ይህ ነው።

ለ. እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ (ቁ. 20-23)

20፥ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥
21፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፡፡
22፥ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
23፥ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ፡፡

... ይህ የተቀደሰ ሃይማኖት ቀደም ሲል በቁጥር 3 ያየነው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠው እምነት ነው። ... ይሁዳ እዚህ የሚለው ይህ አስቀድሞ የተቀበሉት አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠ ሃይማኖት ይዘውት የሚቀመጡት ሳይሆን የሚታነጹበት፥ የሚገነብቡበት እምነት ነው። ... "በዚህ እምነት ወይም ሃይማኖት ራሳቸውን ለማነጽ እንዲተጉ" ያሳሰበው፡፡

ትጋት ከውስጥ፥ ከፍላጎት የሚመነጭ አለመታከትና የመቀጠል አካሄድ ነው። ... ራስን ከማነጽ ጋር ተቆራኝቶ የተጠቀሰውና የትጋት አንዱ ገጽታ የሆነው ጸሎት ነው። "በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ" ይላል። ... ራሱን የሚያንጽ ክርስቲያን ሌሎች እየጸለዩለት በጸሎት ምጽዋት የሚተዳደር ሰው አይደለም፡፡ በጸሎት የሚተጋ እንጂ።

የቁጥር 20 እና 21 ዋናው ግስ 'ጠብቁ' የሚለው ነው። ... ምን ጠብቁ? ራሳችሁን ጠብቁ። በምን ጠብቁ? በእግዚአብሔር ፍቅር ወይም በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ጠብቁ፡፡ ... የእግዚአብሔር ፍቅር የአማኞች ትክክለኛ አድራሻ ነው። ... በፍቅሩ ውስጥ መገኘት አለመጥፋትን ብቻ ሳይሆን አለመናወጥንም ይፈጥራል።

ቁጥር 22 እና 23 የስሕተት አስተማሪዎችን እና በእነርሱ ተጽዕኖ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንዴት መቅረብ እንዳለብን ያሳያሉ፡፡ ... አንዳንዶችን፥ ፈትሻችሁ፥ መርምራችሁ፥ ማንነታቸውን ለይታችሁ ራሩላቸው ነው፡፡ ... "አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥" እነዚህ ሰዎች ለፍርድ የተጻፉ መሆናቸውን አስቀድመን ተመልክተናል። ... ይህ መንጠቅ ትግልን፥ ተጋድሎን፥ ወረራን፥ በጉልበት መውሰድን የሚያሳይ ነው። ዋጋ የሚጠይቅ ገድል ነው፡፡

... "አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ፡፡" ... ሐሰተኛ ነቢያት እና የሐሰት አስተማሪዎች ዘንድ ዘንድ ብዙ የሚያረክሱ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ ... ሥጋቸው ያረከሰውን ልብስ መንካት እንኳ የተጠየፈ መሆኑ ... ርኩሰት ያረክሳል፤ ... ስለዚህ ትልቅ ጥንቃቄ የተገባው ነው።

ቡራኬ (ቁ. 24-25)

24፥ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው፥
25፥ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

ይሁዳ አጭር መልእክቱን የደመደመው በቡራኬ ቃል ነው። ... "ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ።" ... በመንፈሳዊ ጉዞ ውስጥ ብዙ መሰናክሎችና አሳናካዮች አሉ፡፡ ... በዚህ ውስጥ ግን ... ቅዱሳንን ከመሰናከል፥ ከመጠለፍ፥ ከመውደቅ ሊጠብቅ በሚቻለው በእግዚአብሔር እጅ ተጠብቀናል። ይህ ድንቅ ዋስትና ነው።

"በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ፤" ... እኛ በፊቱ የምንቆመው ነን፤ የሚያቆመንም እርሱ ራሱ ነው። ... የፈጠረን፥ በቅዱስ አጠራር የጠራን፥ ያዳነን፥ ያጸደቀን፥ ጸጋን ያደለን፥ በእጁ የያዘን፥ በቀኑ ፍጻሜም በፊቱ የሚያቆመን እርሱ ነው።

"ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን።" እርሱ ብቻውን የሆነ አምላክ ነው። ሌላ ማንም አምላክ ከእርሱ በቀር የለም። ... ይህ አምላክ መድኃኒትም ወይም አዳኝም ነው።

"ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።" ... ይህ ሁሉ ለእርሱ የሚሆነው ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። ... ይሁዳ በመግቢያው ቃል ለቅዱሳን ምሕረት ሰላምና ፍቅር እንዲበዛላቸው የጻፈውንና እዚህ ደግሞ ባለመሰናከል ስለመጥጠበቅና በክብሩ ፊት ስለመቆም የጻፈውን ... ስናጤን ትልቅ እውነት እንጨብጣለን።