አሥር፤ ሃይማኖታዊ እንስታዊነት
ባለፉት ክፍሎች እንዳየነው፥ እንስታዊነት ኅብሩና ፈርጁ ብዙ ነው። ወደ ሃይማኖታዊ እንስታዊነት ስንመጣ ከሃይማኖታዊው ክልል ውጪ ከለዘብተኛው እስከ ጽንፈኛው እንዳለው ሁሉ እዚህም እንደዚያ ነው፡፡ በታሪክ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሴቶች ምንም ስፍራ ተነፍጎአቸው ብቻ ሳይሆን፥ ከሔዋን ጀምሮ ሴቶች የሰይጣን መጠቀሚያ፥ የፈታኝ መሳሪያ፥ የውድቀት ምንጭ እየተደረጉ የኖሩባቸው ዘመናት አያሌ ናቸው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በወንዶች ላይ ለመሠልጠን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ጨቋኝና ጨቋኝነቱም በተባዕታዊ ፆታ የተገለጠ በመሆኑ እግዚአብሔርን ወደ እንስታዊ የመቀየር አዝማሚያም የታየባቸው ሂደቶች ኖረዋል። “በሰማይ የምትኖር አባትእናታችን ሆይ" መባል አለበት ብለው የተከራከሩም ኖረዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር በእንስታዊ ስሜቶች የተገለጠባቸውን ቦታዎች ለምሳሌ፥ ርኅራኄ፥ አዛኝነት፥ ተሸካሚነት፥ ወዘተ፥ በመውሰድ እግዚአብሔርን እንስት አምላክ (Goddess) አድርጎ መጥራትና እንስታዊ ተውላጠ ስሞችን መጠቀም የጀመሩ ኖረዋል፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ ቀለም የተቀባ ጽንፈኛ እንስታዊነት ነው።
በሁለቱ የተራራቁ አመለካከቶች መካከል የሚገኘው ክርስቲያናዊው እንስታዊ ንቅናቄ በአንዳንዶች ዘንድ “ወንጌላዊ እንስታዊነት" የሚባለውና በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ነው። ሃይማኖታዊ እንስታዊነት ሰፊ በመሆኑ እዚህ የማወሳው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትናን ብቻ ነው። ይህኛው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው እውነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፥ ከቃሉ በወጣ፥ ባፈነገጠ መልኩ በወንድ የበላይነትና በባህል ምክንያት የተጫኑ ቀንበሮች መነሣት አለባቸው የሚል ንቅናቄ ነው። ስለ ባህልና እንስታዊነት ቀደም ሲል ተመልክተናል። በባህሎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቃሉ ውስጥም የወንዶች ሚና ምንነትን በትንሹ አይተናል። ይህ ጽሑፍ ሁሉን በትንሽ በትንሽ በማሳየት፥ የማያውቁ በጥቂቱ እንዲያውቁ፥ በስፋት የሚሠሩ ደግሞ እንዲንደረደሩበት ነው።
ክርስቶስ የሴቶችን አርነት በተግባር ያሳየ ጌታ ነው። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሴቶች ነበሩ፡፡ የአገልግሎቱ ደጋፊዎችና የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክሮችም ሴቶች ነበሩ። በዚህ ረገድ፥ የጌታ አገልግሎት የአይሁድን ባህላዊና ልማዳዊ እይታ ተገዳድሮአል። ጌታ ሲያስተምር፥ ቃሉን የሚሰሙና የሚጠብቁ፥ የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉ እነዚህ ወንድሞቹ፥ እኅቶቹና እናቶቹ እንደሆኑ ተናገረ፤ ማቴ. 12፥50፤ ማር. 3፥35። ይህ ትልቅና ድንቅ የሆነ ማቅረብ ነው። ከጌታ ደቀ መዛሙርት መካከል በግልጽ ሴቶች ይኑሩ እንጂ ጌታ ከሴቶች መካከል ሐዋርያት እንዲሆኑ አልመረጠም፤ አልላከም፡፡ ይህ ከወንጌሉ ነው።
ወደ ሐዋርያት ሥራና ወደ መልእክቶች ስንመጣም ተግባራዊ አገልግሎቱ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ጸጋና ፆታ በሚለው ክፍል እንዳየነው ወንዶችም ሴቶችም የአካሉ ብልቶች ናቸው፤ ብልቶችም ሁሉ ተግባር አላቸው። አስተዳደር ወይም አገዛዝና ኃላፊነት ደግሞ ተለይቶ ለወንዶች የተሰጠ መሆኑም በግልጽ ታይቶአል፡፡ ሐዋርያቱ ከጌታ የተቀበሉትን አድርገዋል፤ ቀጣዮቹ አብያተ ክርስቲያናትም ከሐዋርያቱ ያዩትንና የተቀበሉትን አድርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክም ይህን በጉልህ ጽፎታል፡፡
በአንዳንድ የአዲስ ኪዳን ከተሞችና አብያተ ክርስቲያናት፥ ከባህሉም አንጻር የሴቶች ሚና ተጠቅሶ ይህን እንዲያደርጉ፥ ያንን እንዳያደርጉ የተጻፈባቸው ምንባባት የባህልና የወግም፥ የሕግ ወይም የደንብና የሐዋርያት ትእዛዝም የተቆራኘባቸው ናቸው። በıቆሮ. 14፥34-35 በማኅበር ዝም ማለትና መገዛት ለቆሮንቶስ ብቻ ነው ካልን፥ በኤፌሶን አይሠራምና በኤፌሶን የማይተረጐም ልሳን መነገር ይቻላል እንደ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ እኛን ታሳቢ ሳያደርግ እንዲጻፍ አላደረገም። ቀበሌያዊና ባህላዊ ተጽዕኖዎች መኖራቸው እውነት ሆኖ እየተላለፈ ያለው መንፈሳዊ አኗኗርና አገልግሎት ጉዳይ መሆኑም መረሳት የለበትም። ሴቶች ጭቁኖችና የበታቾች አለመሆናቸውን ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች ሲጽፍ አመለከተ፤ በኤፌ. 5፥22 "ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤" ከማለቱ በፊት በቁጥር 21 "ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።" አለ። አንዷ ለሌላው ማለት ነው፤ አንዱ ለሌላዋም ማለት ነው፡፡
በገላ. 3፥26-28 በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውና፥ ከክርስቶስ ጋር የተጠመቁ ወይም አካሉ የሆኑ እርሱን መልበሳቸውን ጽፎ፥ "አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።" ብሎአል። ይህ ሃይማኖታዊ እንስታውያን ወንድና ሴት ብሎ ልዩነት እንደሌለ የሚጠቅሱት ምንባብ ነው። እንደሚጠበቀውም የሚያተኩሩት፥ “ወንድም ሴትም የለም' የሚለው ብቻ ላይ ነው። አይሁዳዊና የግሪክ ሰው፥ ወይም ባሪያና ጨዋ ላይ አይደለም፡፡ ዐውዱን ካልናቅነው በቀር ይህ ክፍል የፆታ ድምሰሳ ምንባብ አይደለም። በእግዚአብሔር ልጅነት ውስጥ እነዚህ ነገሮች አጋጅ አይደሉም ማለት እነዚያ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አይሁዳዊና ግሪኩ ትውልዳቸው አልተሰረዘም። ክርስቲያን ባሪያ ጌታውን፥ 'እኔና አንተ እኩል ነን' ብሎ ባርነቱን አልሰረዘም። ባርነት ከቶም አልቀረም። ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት መልክ ነው የተቀየረው፡፡
ሴትና ወንድ ሲልም ፆታው አልቀረም፤ ሚናውም አልተቀየረም። የእግዚአብሔር ጸጋ አብሮ ወራሽ ተሆነ፡፡ ክፍለ ምንባቡ ስለ አብርሃም ልጅነትና የተስፋው ወራሽ ስለመሆን ነው የሚናገረው። በውስጣዊው ዘላለማዊው ማንነት አንድና እኩልታን የተጎናጸፍን ፍጡራኑና ልጆቹ ነን። ያ አካላዊ ማንነታችንን እና ፆታዊ ሚናችንን፥ በቃሉ መሠረት የተሰጠንን ጸጋና ሥልጣን ግን አይለውጠውም፡፡
ሴቶች የተሰጣቸውን ያንን ጸጋ ቃሉ በሚፈቅድላቸው መስመር ሊወጡት መንገድ የለም የሚሉ ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው። ወንዶችም ወንዶች ስለሆኑ ብቻ ያገለግላሉ ማለት አይደለም። ጸጋና ፆታ በሚለው ክፍል እንዳየነው ሴቶች የማስተማር ጸጋ ካላቸው የሚያስተምሩባቸው እልፍ መንገዶች አሉ። “ከማን አንሳ ይህኛው መድረክ ይከለከላታል? ማለት መድረኩን ሳይሆን የፍላጎቱን ምንጭ ያመለክታል። ቃሉ እንደየባህላችንና እንደ ዘመናችን መልክ እያመሳሰልን የምናጠጋጋው ሳይሆን፥ ቃሉ ባህላችንን የሚቀርጽ መቅረጫ ነው፡፡
ቃሉ ባህላችንን እና ፍልስፍናችንን መምሰል የለበትም፥ በተቃራኒው ባህላችንና ፍልስፍናችን ነው ቃሉን መምሰል ያለበት፡፡ እንስታዊነት ለቃሉ መገዛት አለበት እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እንስታዊነትን መምሰል ወይም ለመምሰል መልለወጥ የለበትም፡፡ ሴቶች የግድ በጉባኤ በመሪነት ላይ ሆነው ሰዎችን በመምራት ሳይሆን በውስን መልኩ ሴቶችን በመምራትና በማስተማር ማገልገላቸው ውበታቸው እንጂ ከቶም የበታችነት አይደለም። ከቶም።
በቤተ ክርስቲያንም የሴቶች መሪነትና ቅስና ንቅናቄ የተጀመረው ከጥንት ሳይሆን ከ1960ዎች የአርነትና እንስታዊነት ንቅናቄ በኋላ ነው። ተከትሎት የመጣው የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሕጋዊ የመሆን ጥያቄም፥ ኃጢአቱ ቀድሞም የነበረ ቢሆንም ዘሩ የተዘራው በተለይ ከጽንፈኛ እንስታዊነት ጋር ተያይዞ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሁሌም የማይለወጥ መሪ ቃል ያላት በዓለቱ ላይ የተመሠረተች አካል ናት እንጂ በየዘመናቱ በሚመጡ (እንስታዊ ንቅናቄንም በሚጨምር) ንቅናቄዎች የፊት አቅጣጫዋ የሚለዋወጥና በነፋስ የምትገፋ መርከብ አይደለችም። የእንስታዊነት ንቅናቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡
ተፈጸመ፡፡