የህይወት ቃል ህብረት Logo

የዘመናችን 'ሐዋርያዎች' ኢየሱስ

'ሐዋርያ'ፖዝ እና የሚሰብከው ኢየሱስ

በ ዘላለም መንግሥቱ

መግቢያ

በApril 2016 መጀመሪያ አንድ ማታ ከጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነን በExodus TV Show (ቤተልሔም ታፈሰ) የተዘጋጀ የሐዋርያ ዘላለም (ፓዝ) ጌታቸው ተከስተን (ከዚህ በኋላ ሐዋርያ ፖዝ ወይም ፖዝ) ቃለ መጠይቅ ተመለከትን። ... በቃለ መጠይቁ ውስጥ ተጠያቂው ገሃድ ያደረጋቸው ጉልህ የስሕተት ትምህርቶች በቀላሉ መታየት የሌለባቸው መሆናቸውን ራሳቸው የሚገልጡ ናቸው።

... በጽሑፉ የማቀርበው ባገጠጡት ስሕተቶች፥ በተለይም አስተምህሮታዊ በሆኑቱና በኢየሱስ ማንነት ላይ በተቃጡቱ ላይ ብቻ ነው። ... በቃለ መጠይቁ ውስጥ ይህ ሰው ኢየሱስን አራት ነገሮች አድርጎ አሳይቶአል። እነዚህ አራት ነገሮች፥

  1. ፖዝ አድራጊ/አስደራጊ (ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ)፣
  2. የሰየጠነው/ሰይጣን የሆነው (ሰይጣኑ ኢየሱስ)፤
  3. ሰው ብቻ/ሰው ብቻው (ሰውየው ኢየሱስ)፤
  4. ታጃቢ (ታጃቢው ኢየሱስ)።

... 'እነዚህ እንደ ፖዝ ያሉት ሰዎች የሚናገሩት ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ነው ወይስ እነርሱ የፈጠሩት ኢየሱስ?' ብሎ መጠየቅ ተገቢና የመልሳችን መዝገብ ወደሚገኝበት ወደ ቃሉ እንድንሄድ የሚያደርገን ጥያቄ ነው፡፡ ... ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮ. 11፥4 "የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።" ያለው ያኔም አሁንም እውነት ነው፡፡ ሌላ ኢየሱስ፥ ልዩ መንፈስ፥ ልዩ ወንጌል። ይህ ታዲያ የሚታገሡት ትምህርት መሆን የለበትም።

1. ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ?

ፖዝ ከሚለው ቃል ልጀምር። ሐዋርያ ዘላለም የቅጽል ስሙ ፖዝ (pause) መሆኑን ይናገራል። ... ሐዋርያ ፖዝ ስሙ ለምን ፖዝ እንደተባለ በቃለ መጠይቁ ሲናገር፥

"እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የድህነትን፥ የኃጢአትን፥ የሞትን፥ የበሽታን አካሄድ ፖዝ አርጓል፤ አቁሟቸዋል። ... ፖዝ ታረግልኛለህ ሲል ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ታደርጋለህ፤ ባይ ዘ ዌይ፥ ፖዝ ማለት የቃሉ ፍቺ፥ ማቆም ማለት ነው። ... ፖዝ ማለት ጳውሎስ ማለት ነው። ... ጌታ ያለኝ በቀጥታ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በዚህ ትውልድ መሐል ለኔ ጳውሎስ ነህ ነው ያለኝ። ... ጳውሎስ የሚለው ፊደል የግሪክ ቃል ላይ ሄጄ ሳጠናው ... ሩት ወርዱ ምን ይላል? ፖዝ ይላል። ... [ሐዋ. 13፥8-11] ... እስከ ጊዜው ፀሐይን አታይም አለው። በሌላ አማርኛ ሰውየውን ምን አረገው? ፖዝ አረገው። ጳውሎስ ፖዝ ነው። ጳውሎስ ማለት ፖዝ ማለት ነው።"

ይህች ናት ትርጎማ! ... ይህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችንም ያላሉትን እንዲል እያደረገ ሊፈታ የሚሞክረው በዚህ መንገድ መሆኑን ዝቅ ስንል እናየዋለን።

ጳውሎስ የግሪክ ሳይሆን የሮማይስጥ ቃል ነው። ስም ሳይሆንም ቅጽል ነው፤ እንዳለውም ትርጉሙ ትንሽ፥ ታናሽ ማለት ነው። ... ጳውሎስ ማለት ፖዝ ማለት ነው፤ እኔ ጳውሎስ ነኝ ስለዚህ እኔ ፖዝ አድራጊ ነኝ ማለት ከአፈታትና አገነዛዘብ ደንብ የተፋለሰ ብቻ ሳይሆን ብልሹ አፈታት ነው።

... ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ ፖዝ አላደረጋቸውም። እነዚህ ነገሮች (ድኅነት፥ ኃጢአት፥ ሞት፥ በሽታ፥ ጨለማ) አልቆሙም። ... ፖዝ እኮ አልተደረጉም! ገናም ጌታ ከርስቶስ ዳግም እስኪመጣና እስኪወስደን ድረስ በጋና ክረምት እንደሚኖሩ እነዚህ ነገሮችም መኖራቸው ይቀጥላል።

ፖዝ አስደራጊው የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታና መድኃኒት ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ከምድር ላይ እንደሚወገዱ ... አልተናገረም። በምድር ሳለን መከራ እንዳለብን ነው ያስተማረን። ... ፖዝ pause እንዳደርግ ነገረኝ የሚለው ኢየሱስ ማን መሆኑ መጠየቅ ያለበት ትልቅ ጥያቄ ነው። በመስቀል ላይ የሞተልን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ እንዲህ የመሰለ ቅሌታም ሹመትና ፌዘኛ ሹም የሚሾም ንጉሥ አይደለም።

2. ሰይጣኑ ኢየሱስ?

ኢየሱስ ሰየጠነ (ወይም ሰይጣን ሆኖ ነበር) ወይ? ለሚለው ጥያቄ ... በእርግጥ ኢየሱስ እንደሰየጠነ ሲጠየቅ፥

"'ዘላለም ሰይጥኗል ኢየሱስ ትላለህ' ብለው ማቴቴስ ላይ አውጥተውኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ያንን ቃል በቀጥታ ኢየሱስ ሰይጥኗል ሚለውን አልተጠቀምኩም። ግን፥ ቃሉ የሚናገርበት ... 'ይሄ እኮ ማለት ከባድ ነገር አይደለም፤ ... [ኢየሱስ] 'እርግማን ሆኜ፥ ኃጢአት ሆኜ፥ የግብጽ የበኩር ልጅ ሆኜ ሞቼላቸዋለሁ፡፡' ሆኜ ነው ያለው። ... አምላከ እርግማን ይሆናል? አምላክ ኃጢአት ይሆናል? አምላከ የኃጢአት ኔቸር አለው? ... [ሰየጠነ የሚለውን] ይህንን ቃል የተጠቀሙት ሌሎች ናቸው። የነ ኬንዮን፥ የሌላ ፌይዝ ላይ ያሉ ሰዎች ያሉት ነው። ግን ያሉትም ቢሆን ብዙ ስሕተት አይደለም።"

ትምህርቱ ተጠምዝዞ እዚያው የተሽከረከረው ቃሉን አላልኩም እያለ ትምህርቱን፥ ማለትም፥ ከርስቶስ ሰየጠነ የሚለውን ትምህርት ግን ስለሚቀበል ነው:: ... 'እነዚያ ኢየሱስ ሰየጠነ ያሉት ብዙም ስሕተት አይደለም' ማለት ብዙ እውነት ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ሰየጠነ ማለትን በትክክል ይቀበላል ማለት ነው።

"ጴጥሮስን እስከመሰጠን ያወረደ ቃል ካለ ጴጥሮስን ለመቤዠት ጌታዬ ልከ እርግማን እንደሆነ እዚህ ድረስ ወረደ ብል ኢየሱስ ሰይጣን ነው እያልኩ አይደለም፤ ሊቤዠው ሰውየው እስከወረደበት ጥግ ወርዷል እያልኩ ነው።"

ፖዝ ከላይ በተወሰደው ከፍል ... 'በእርግጥ ጴጥሮስ ሰይጥኖ ነበር ወይ?' የሚለው ነው። እንደ ፖዝ ... ጴጥሮስ የሰየጠነ ሲሆን ኢየሱስ ጴጥሮስን ከሰየጠነበት ለማውጣት መሰይጠን ኖሮበታል ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ ሰይጣን ሆነ ወይም የሰይጣንን ባሕርይ ተላበሰ የሚለው ትምህርት በፖዝ የተጀመረ አይደለም፤ ... ፖዝ የሚነዛው የትምህርቱ ዋና አቀንቃኝ የሆነውን አሜሪካዊውም ዊልያም ኬንየንን መርዘኛ ትምህርት ነው።

ቤኒ ሂን፥ 'He [Jesus] who is righteous by choice said, "The only way I can stop sin is by Me becoming it. ... He who is the nature of God became the nature of Satan where He became sin!"' ... 'የእግዚአብሔር ባሕርይ የነበረው ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ በመውሰድ ኃጢአት ሆነ፡፡' ይህ የቤኒ ሂን ትምህርት ነው። ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ መውሰዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም።

የቃል-እምነት አስተማሪዎች፥ 'ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ ስለተጋራ ዳግም መወለድ አስፈልጎት ነበር፤ በሞቱና በትንሣኤው መካከል ነው ይህን ዳግም ልደት ያገኘው' ይሉናል። ... ፖዝ ... 'ቢሆንስ ምን ያስገርማል?' ወደ ሰይጣን ጎራ የምታስገባ ታናሽ እርምጃ ናት፤ ግን ከትንሿ እርምጃ ቀጥሎ ትልቅ ዝላይ መጠበቅ እንችላለን። ይህ ያፈጠጠ የስሕተት ትምህርት ነው።

3. ሰውየው ኢየሱስ?

ኢየሱስ እንደ ሰው ብቻ ነው የተመላለሰው? ፖዝ ይህን በግልጽ ተናግሮአል። ይህ ጠማማ የስሕተት ትምህርት ኢየሱስ በምድር በተመላለሰባቸው 33 ዓመታት ከቶም አምላክነቱን አልገለጠም፥ አልተለማመደም፥ ... እንደ ፍጹም ሰው ብቻ ሆኖ ነው ትምህርቶቹን ያስተማረውና ተአምራቱንም ያደረገው የሚል ... ስሕተት ነው።

"... ጌታ ኢየሱስ ... ሰው ሲሆን ከርስቶስ ሁለተኛ አዳም ነው የሆነው። እግዚአብሔር ሆኖ አይደለም በምድር የተመላለሰው። እግዚአብሔርነቱን እያሳየ አይደለም በምድር የሠራው:: ... ከርስቶስ በምድር ላይ መለኮታዊ ማንነቱን አልተጠቀመም። የተመላለሰው በሰው ማንነት፥ በመንፈስ ቅዱስ ቅባትና ኃይል ነው።"

... ፖዝ የሚነግረን ኢየሱስ 'ሰውየው ኢየሱስን' ነው። ... ጌታ ኢየሱስ ... ሰው ብቻ ነበረ፤ እንዲያውም ከሰውም የወረደና የሰየጠነ ነበረ ይለናል። ... ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበረ ማለት አንድ ባሕርይ ብቻ ነበረው ማለት ነው። መለኮታዊነት የሌለው ሰብዓዊ ብቻ የሆነ ነው ማለት ነው።

"በምድር ላይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ አልተመላለሰም። አሁን በሰማይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው። ዱሮ ወደ ምድር ሳይመጣ በፊት ፍጹም አምላክ ብቻ ነበር። በምድር ላይ ቤዛ ሲሆን በሰው ማንነት ሁለተኛው አዳም ሆነ።"

ከዚህ የፖዝ የድፍረት ንግግር በግልጽ የምንረዳው ከመምጣቱ በፊት ፍጹም አምላክ፥ አሁን ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደሆነ ሲሆን፥ በመካከል ግን መለኮትነት የሌለው ፍጹም ሰው ብቻ እንደነበር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ኢየሱስ ሥጋ የለበሰ እግዚአብሔር ወልድ ነው። ያ የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው ሥጋ የለበሰው። ... ኢየሱስ አንድ አካል ነው፤ በዚያ አንድ አካል ውስጥ ሁለት ባህርያት አሉ። ኢየሱስ በአንድ አካል ፍጹም ሰው እና ሙሉ አምላክ ሆኖ ተመላልሶአል። አንድ አካል ሁለት ባሕርያት፡፡

ፖዝ የሚነግረን ኢየሱስ አንድ አካልና አንድ ባሕርይ ኢየሱስ ነው። ፖዝ ሊመልስልን የሚገባው የሥላሴ ሁለተኛ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ በሥጋ በተመላለሰባቸው 33 ዓመታት የት ነበር?

4. ታጃቢው ኢየሱስ?

ኢየሱስ በአጃቢዎች እየተከበበ ይመላለስ ነበር! ... ፖዝ አንድ ስፍራ ላይ ሊናገር እንደሞከረው ይህ የመታጀብ ጉዳይ ... ትክክል መሆኑን መናገሩና ታጅቦ መሄዱን ለማጽደቅ ... ምሳሌ አድርጎ ኢየሱስን በመጥቀሱ ነው ልናገርበት የምፈልገው።

"መጀመሪያ በጋርድ የሄድኩት እኔ ነኝ። ... በጋርድ መሄድ ምንድነው ፐርፐዙ? ... ደግሞስ ሲቀጥል፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? ጌታ ኢየሱስጋ ሰዎች ሕጻናት ልጆች ይዘው መጡ ይላል። ደቀ መዛሙርቱ ከለከሏቸው ይላል። ጌታ ኢየሱስ አትከልክሏቸው አለ ይላል። በሌላ አማርኛ ጌታ ኢየሱስጋ ማንም ሰው ከመድረሱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ይከለከሉ ነበር ማለት ነው።"

ፖዝ ኢየሱስ ታጅቦ ይሄድ እንደነበር ዋና ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው ሐዋርያቱ ሕጻናትን መከልከላቸውን ነው። ... በሦስቱም ወንጌላት እነዚህ ከፍሎች ሕጻናትን እንዲዳስሳቸው ወደ እርሱ ማምጣታቸውን፥ ሕጻናቱም ኢየሱስ ዘንድ መድረሳቸውን እንጂ ለማምጣት ከአጋፋሪዎች ጋር ግብግብ መግጠማቸውን አይናገሩም።

... "ማቴዎስ፤ ... ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው፡፡" ... ካመጡ በኋላ ነው ደቀ መዛሙርቱ ያመጧቸውን ሰዎች የገሠጹት እንጂ ሳያመጡ ከሩቅ አላገዷቸውም። ኢየሱስን እንደ ክብር ዘብ ሆነው አልከለሉትም።

... ዛሬ በአጃቢ የሚሄዱ ሐዋርያትና ነቢያት ተብዬዎች መኖራቸው አያስደንቅም። ... የሚያስደንቀው እና ይልቁንም የሚያሳፍረው ግን ኢየሱስንና የኢየሱስን ሐዋርያት የዚህ ስንፍናቸው ምስከር አድርገው ሲጠሩ ነው፡፡ ኢየሱስ ታጃቢ አልነበረም።

መደምደሚያ

መሆንና ማድረግ። የሐዋርያ ፖዝ ስሕተት ዋና አደጋ ኢየሱስ ሰው ብቻ ሆኖ ስለተመላለሰ እርሱ የሆነውን እንሆናለን ወይም ያደረገውን እናደርጋለን የሚል ነው። የሆነውን መሆን እንደማንችል በግልጽ የታወቀ ነው። ... እኛ ሰውነታችንን ይዘን ወይም ጥለን መለኮት እንሆናለን ማለት የሐሰት ትምህርት ነው።

... ጌታ ኢየሱስ አምላክ የሆነውን ማንነቱ አውልቆ አንድ ስፍራ ደብቆ አስቀምጦ በሰውነቱ ስብዕና ብቻ አልተመላለሰም። ... ጌታ ግን በሚያገለግልበትና በሚያስተምርበት ጊዜ ማንነቱን አልደበቀም። አይሁድ ሲከስሱትና እንዲሰቀል ሲያደርጉት ሰው ብቻ መሆኑን ተናግሮ ከመሰቀል በተረፈም ነበር።

... ምልክቶችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ናቸው ብለን መቀበል ስሕተት ነው። ሰይጣንም ምልክቶችን ሊያደርግ እንደሚችል መታወቅ ሊቅነትን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆን የለበትም። ማቴ. 7፥22-23 ... "ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ ... ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።" ...

መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮቶች የከበረ ስፍራ በሰው ሠራሽና በአጋንንታዊ ትምህርቶች እንዳይለወጡ ትጉሃን የቃሉ ተማሪዎች ልንሆን ይገባናል። ... እግዚአብሔር ከስሕተት ትምህርቶችና አስተማሪዎች፥ ከአጋንንታዊ አሠራሮች፥ ከአሳች ትምህርት ዐውሎ ነፋሶች እና ከክፉ ሠራተኞች ይጠብቀን።

አሜን።