የህይወት ቃል ህብረት Logo
Trinity

የሥላሴ አስተምህሮ

የሥላሴ ትምህርት የክርስትና እምነት የማዕዘን ድንጋይና እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት እውነት ነው። ይህ ትምህርት የሂሳብ ቀመር ወይም የፍልስፍና እንቆቅልሽ ሳይሆን፣ የሕያው እግዚአብሔርን ውስጣዊ ማንነት፣ ባህርይና የፍቅር ሕይወት የሚገልጽ መለኮታዊ ምስጢር ነው። በቀላል አነጋገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረው አምላክ አንድ አምላክ ሆኖ፣ በዚህ አንድ መለኮታዊ ማንነት ውስጥ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በመባል የሚታወቁ ሦስት፣ እኩልና ዘላለማዊ አካላት መኖራቸውን ነው።

ይህ ማለት ሦስት አማልክት አሉ ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ አንድ መለኮታዊ ምንነት በሦስት ልዩ አካላት ይኖራል ማለት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውና የማይናወጥ እውነት "እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው" (ዘዳግም 6:4) የሚለው ነው። የሥላሴ ትምህርት ይህንን እውነት በማጽናት፣ የዚህን አንድ አምላክ ውስጣዊ ማንነት በዝርዝር ይገልጻል።

የመለኮት ባህርይ (Godhead)

“መለኮትነት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ በእርሱ ይኖራልና።” — ቆላስይስ 2፡9

መለኮት (Godhead)

መጽሐፍ ቅዱስ የማይታየው አምላክ መለኮታዊ ባህርዩን በፍጥረቱ በኩል እንዳስታወቀ ይገልጻል። ጳውሎስ በሮሜ 1፡20 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “ማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” መለኮትነት የሚለው ቃል በጥሬው መለኮታዊ ባህርይ ማለት ሲሆን፣ በፍጥረት ውስጥ የሚታየውን የእግዚአብሔርን ዘላለማዊና ኃይለኛ ምንነትን ያመለክታል።

በሐዋርያት ሥራ 17፡29 ላይ ጳውሎስ፡- “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም።” በዚህ ቃል ጳውሎስ መለኮት ቁስ አካል ወይም ሕይወት የሌለው ሳይሆን ሕያውና መንፈሳዊ መሆኑን በማጉላት የጣዖት አምልኮን ይቃወማል።

በቆላስይስ 2፡9፡- “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።” ይህ ኃይለኛ ጥቅስ የመለኮት ሙላት በክርስቶስ በሰውነት ተገልጦ እንደሚኖር ያረጋግጣል። የማይታየው አምላክ የመለኮትነትን ሙላት ሙሉ በሙሉ በያዘው በኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት በግልጽ ተገልጧል።

የአንዱ እውነተኛ አምላክ አንድነት

ከብሉይ ኪዳን እስከ አዲስ ኪዳን ድረስ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ አጥብቀው ይናገራሉ። ዘዳግም 6፡4 እንዲህ ይላል፡- “ስማ እስራኤል ሆይ! አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው።” ይህ መሠረታዊ የአሐዳዊነት እውነት የእግዚአብሔርን ሦስትነት ለመረዳት መንገድ ይከፍታል።

ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን መለኮታዊ አንድነት ደጋግሞ ገልጿል፡- “እኔ ፊተኛው ነኝ፣ እኔም መጨረሻው ነኝ፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም።” (ኢሳይያስ 44፡6) ከዚህም በላይ ኢሳይያስ 45፡18 እግዚአብሔር ብቻ ፈጣሪ መሆኑን ያረጋግጣል፡- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ሌላም የለም።” ኢየሱስ ራሱም ይህንኑ እውነት አስተጋብቷል፤ በዮሐንስ 4፡24 ላይ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” በማለት ይገልጣል።

እነዚህ ጥቅሶች በሙሉ የእግዚአብሔርን አንድነትና ልዩነት ያረጋግጣሉ። ሆኖም፣ በዚህ አንድነት ውስጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሦስት አካላትን ያካተተ እውነታን ይገልጻል፡- "አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ"።

አንዱ አምላክ ሦስት አካል ያለው መገለጥ

አብ እግዚአብሔር ነው፡፡ አብ የሁሉ ነገር መሠረትና ምንጭ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡6 እንዲህ ይላል፡- “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥”። ኤፌሶን 4፡6 ደግሞ፡- “አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉ የሚሠራና በሁላችንም የሚኖር ነው።”

ወልድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ወልድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መለኮታዊ ማንነት ሙሉ በሙሉ ይካፈላል። ዮሐንስ 1፡1 እንዲህ ይላል፡- “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋራ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።” ቶማስም “ጌታዬና አምላኬ!” (ዮሐንስ 20፡28) በማለት መስክሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን “ታላቁን አምላካችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን” (ቲቶ 2፡13) ብሎ በመጥራት ፍጥረት ራሱ በእርሱ እንደሆነ ይገልጻል፡- “በሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩና የማይታዩ፣... ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአልና።” (ቆላስይስ 1፡16–17)።

መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መለኮታዊ ነው። ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ 5፡3–4 ላይ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት እግዚአብሔርን መዋሸት እንደሆነ ይናገራል። 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡17 “ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ።” በማለት ያረጋግጣል፣ እንዲሁም 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10–11 መንፈስ ብቻ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንደሚያውቅ ያሳያል።

የሦስትነት ጥቅሶች

በኢየሱስ ጥምቀት ወቅት (ማቴዎስ 3፡16–17)፣ ወልድ ተጠመቀ፣ መንፈስ እንደ ርግብ ወረደ፣ አብም ከሰማይ ተናገረ። ታላቁ ተልእኮ አማኞችን “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲያጠምቁ ያዛል (ማቴዎስ 28፡19)።

ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን በሦስትነት በረከት ይባርካታል፡- “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋራ ይሁን።” (2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14)።

ሦስቱም አካላት የሚጋሩት መለኮታዊ ባሕርያት

እያንዳንዱ የመለኮት አካል ተመሳሳይ መለኮታዊ ባሕርያትን ይጋራሉ። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በእኩልነት፣ በዘላለማዊነትና በዘላቂነት አብረው የሚኖሩ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

መለኮታዊ ባሕርይ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ
ዘላለማዊነት መዝሙር 90፡2 ዮሐንስ 1፡1–2 ዕብራውያን 9፡14
ፈጣሪነት ዘፍጥረት 1፡1 ዮሐንስ 1፡3 ኢዮብ 33፡4
ሁሉን መገኘት ኤርምያስ 23፡24 ማቴዎስ 28፡20 መዝሙር 139፡7
ሁሉን አዋቂነት 1ኛ ዮሐንስ 3፡20 ዮሐንስ 16፡30 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10–11
ቅድስና ራእይ 15፡4 ሐዋ. ሥራ 3፡14 ኤፌሶን 4፡30
እውነት ዮሐንስ 7፡28 ዮሐንስ 14፡6 ዮሐንስ 14፡17
ሕይወት ሰጪነት ዘፍጥረት 2፡7 ዮሐንስ 5፡21 ሮሜ 8፡11

እነዚህ በጋራ የሚገለጹ መለኮታዊ ባሕርያት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮታዊ ባህርይ እንዳላቸው—በእኩልነት፣ በዘላለማዊነትና በዘላቂነት አብረው የሚኖሩ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

መለኮትነት (The Godhead) የሚያመለክተው በሦስት የተለያዩ አካላት የተገለጠውን አንድ መለኮታዊ ማንነት ነው። ኢየሱስ፡- “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐንስ 10፡30) በማለት አንድነትን አውጇል።

እግዚአብሔር በመሆን አንድ፣ በአካል ግን ሦስት ነው። ፍጹም የሆነ ሦስትነት ነው፡- "አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ"።

በድነት፣ አብ ያቅዳል፣ ወልድ ይፈጽማል፣ መንፈስም ቤዛነትን ተግባራዊ ያደርጋል። በጸሎት፣ “በአንድ መንፈስ ሁላችን ወደ አብ መቅረብ ተችሎናል” (ኤፌሶን 2፡18)። በመቀደስ፣ መንፈስ ቅዱስ “የርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር ይለውጠናል” (2ኛ ቆሮንቶስ 3፡1)።

የሦስትነት ትምህርት ፍልስፍናዊ ግምት ሳይሆን መለኮታዊ መገለጥ ነው። መለኮት በምነነት አንድ፣ በአካል ሦስት ነው፤ በእኩልነት፣ በዘላለማዊነትና በዘላቂነት አብረው የሚኖሩ ናቸው።

“ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” ሮሜ 11፡36

ሥላሴ በፍጥረት

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።” ዘፍጥረት 1፥1-3

የፍጥረት ምስጢር በዘመናት መጋረጃ ሲገለጥ

ጊዜ የመጀመሪያውን ሰከንድ ከመቁጠሩ በፊት፣ ከዋክብትም ከመታሰባቸው አስቀድሞ፤ ያልተጀመረው፣ ያልተፈጠረውና ወሰን የሌለው እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ ከክህሎቱ በላይ አንዳች የሌለ፣ ያለድካም የሚሠራ፣ ያለሕልፈት ህልው የሆነ፣ ያለጊዜ የሚኖርና ያለመታከት የሚመራ አምላክ ነው። ይህ አምላክ "መጀመሪያ" በሚባል ጊዜ አጽናፈ ዓለሙን ካለመሆን ወደ መሆን አምጥቶታል። እርሱ የሁሉም ነገር ምንጭና አባት ቢሆንም፣ አባትነቱ ግን ከፍጥረትም በፊት የነበረ ነው፤ ከእርሱ ዘንድ የዘላለም ሕያው ቃል ተገኝቷልና።

የ "ኤሎሂም" (Elohim) ሰዋሰዋዊ ምስጢር

ዕብራዊው ጸሐፊ ሙሴ የዘፍጥረትን መጽሐፍ ሲጀምር “ኤሎሂም ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ይለናል። ሙሴ 'ኤሎሂም' የሚለው ቃል የብዙ ቁጥር አመልካች መሆኑን አልዘነጋውም፤ ነገር ግን “አማልክት ሰማይንና ምድርን ፈጠሩ” ከማለት ይልቅ፣ ከቋንቋ ሕግ ውጪ በብዙ ቁጥር አመልካች ባለቤት “ኤሎሂም” ብሎ ዓረፍተ ነገሩን ጀምሮ፣ በአንድ ቁጥር አመልካች ግስ “ፈጠረ” ብሎ ይቋጨዋል። ይህ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ከፍጥረት መባቻ ጀምሮ የእግዚአብሔርን ሦስትነትና አንድነት (ሥላሴን) ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ታሪካዊ ማረጋገጫ ነው።

የሥላሴ መለኮታዊ ኅብረት በፍጥረት ሥራ

አብ የፍጥረት ምንጭ

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ቃላት፣ የፍጥረት የጅማሬ መጋረጃን ሲከፍቱ የሚያሳዩን የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም ስምምነት ነው። እግዚአብሔር አብ የፍጥረት ሁሉ የመጨረሻ ምንጭና መለኮታዊ አውጪ (Architect) ነው። የፍጥረት ዕቅድና ዓላማ ከእርሱ ይነሳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ ከእርሱ፣ በእርሱም፣ ለእርሱም ነውና” (ሮሜ 11:36) እንዳለው፣ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር…” የሚለው ቃል በዋነኛነት የሚያመለክተው ይህንን አስጀማሪ የሆነውን አብን ነው።

ወልድ የፍጥረት ፈጻሚ (ቃል)
የሂ (Yehi) / አሜን

እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው በድካም ሳይሆን፣ ቃሉን በመናገር ብቻ ነው። “ይሁን” (በዕብራይስጡ - የሂ) የሚለው ቃል የምኞት መግለጫ ሳይሆን መለኮታዊ ድንጋጌ ነው። ይህ ድምፅ ብቻ አይደለም፤ ከዘላለም ጀምሮ ከአብ ጋር የነበረው “ቃል” (ሎጎስ)፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሐዋርያው ዮሐንስ “አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር” (ራእይ 3:14) ይለዋል። አብ “ብርሃን ይሁን” ብሎ ሲያውጅ፣ ያንን አዋጅ ወደ መኖር ያመጣው ሕያው “አሜን” የሆነው ወልድ ነው። አብ አሰበ (ነደፈ)፤ ወልድ ደግሞ ያንን መለኮታዊ ንድፍ ወደ እውነታ የቀየረ ዋና መሐንዲስ ነው። የድሮውን ፍጥረት በቃሉ ያጸናው እርሱ፣ ዛሬም በአማኞች ሕይወት አዲስ ፍጥረትን የሚፈጥረው እርሱው ነው።

መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሰጪ (እስትንፋስ)
ራኻፍ (Rakhaf) / ሩአክ

ምድር “ቅርጽ የለሽና ባዶ” በነበረችበት ጊዜ፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” (ዘፍጥረት 1:2)። “ሰፍፎ” ተብሎ የተተረጎመው ራኻፍ የሚለው የዕብራይስጥ ግስ ሲሆን፣ ንስር በጫጩቶቿ ላይ እንደምትረብብ (ዘዳ 32:11) መንፈስ ቅዱስም ሕይወትን ለመስጠትና ለማሳደግ በውኃው ላይ መስፈፉን ያሳያል።

በመዝሙር 33:6 ላይ የተጠቀሰው “የአፉ እስትንፋስ” (በዕብራይስጡ ሩአክ) መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። ሰማያት የአብን ጥበብ፣ በወልድ ኃይል ተፈጥረው፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ተሞልተው ይመሰክራሉ። ስለዚህም አምልኳችንና ምስጋናችን ለዚህ ሦስትነትና አንድነት ላለው አምላክ ይገባል።

የብሉይ ኪዳን ምስክርነት

“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር...” ዘፍጥረት 1፥26

እግዚአብሔር ከማን እየተማከረ ይሆን? “ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው?” (ኢሳ 40፥ 14) ይላል። እግዚአብሔር ከገዛ ራሱ ጋር ከገዛ ከመንፈሱ ጋር እንዲሁም ከገዛ ቃሉ ጋር እየመከረ ነው። ለዚህም ነው ሙሴ ከመቅጽበት “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ 1፥27) በማለት እግዚአብሔር ራሱን እንደብዙ በመጥራት እያከበረ አለመሆኑን ግልጽ አድርጎልናል።

“እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ...” ዘፍጥረት 3፥22

አዳምን ‘እንደ መልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር’ ያለ አምላክ ፥ አሁን ደግሞ ‘አዳም መልካም እና ከፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ’ እያለ ነው። ይህ ብዝኸነት አመልካች ነው። እግዚአብሔር አብ፥ ደግሞም የእግዚአብሔር ቃል እንዲሁም የእግዚአብሔር መንፈስ ከራሱ መከረ፤ ‘ሰው ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ’ አለ።

“ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።” ዘፍጥረት 11፥7

እግዚአብሔር ‘ኑ እንውረድ…ቋንቋቸውንም እንደባልቀው’ የሚለው ማንን ይሆን? ይህም ክፍል የሚያሳየን በእግዚአብሔር አብ፥ በእግዚአብሔር ቃል እና በእግዚአብሔር መንፈስ መሐል የተደረገ የራሱ የእግዚአብሔር ምክር መሆኑን ነው።

የጌታ መልአክ

በብሉይ ኪዳን ውስጥ “የጌታ መልአክ” ተብሎ የሚጠቀሰው አካል መለኮታዊ ሥልጣንና ባሕርይ እንዳለው ሆኖ ቀርቧል። ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ራሱ ጋር በተለዋዋጭነት ይጠቀሳል።

“የእግዚአብሔርም መልአክ በቁጥቋጦው መካከል በእሳት ነበልባል ታያት... ሙሴም፦ እግዚአብሔርም በቁጥቋጦው ውስጥ ሆኖ። ሙሴ፥ ሙሴ፥ ብሎ ጠራው።” ዘጸአት 3:2, 4

በዚህ ክፍል መጀመሪያ ላይ የታየው "የጌታ መልአክ" እንደሆነ ተገልጿል፤ ነገር ግን የሚናገረው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይህ ሥጋ ከመልበሱ በፊት የነበረውን ክርስቶስን (ወልድን) የሚያመለክት እንደሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ያምናሉ።

ይህን ሁሉ ከተናገረ በኋላ ሙሴ ለእስራኤል እንዲህ ብሎ ያስተዋውቀዋል፤

“እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው።” ዘዳግም 6፥4

አዎ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮናል፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ከእግዚአብሔር አብ የተለየ አምላክ አይደለም። አዎ በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸንተዋል የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር መንፈስ የተለየ ሁለትኛ ወይም ሦተኛ እግዚአብሔር አይደለም። አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው።

የአዲስ ኪዳን ምስክርነት

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ኢሳይያስ 9፥6

ይህ ትንቢት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽሟል። ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሲናገር፦ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ... ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐ 1፥1, 14)

የጌታችን እናት

“ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” ሉቃስ 1፥41-43

ማርያም ‘እግዚአብሔር ነበረ’ ለተባለው ፥ ‘አንድ ጌታ’ ለተባለው ለኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ እናቱ ሆነች። እግዚአብሔር ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ አምላክነቱ ከሰብአዊነቱ ሳይቀላቀል ደግሞም ፈጽሞ ሊነጣጠል በማይችል ሁኔታ አንድ አካል ፥ አንድ ሰው ክርስቶስ ሆነ። ስለዚህ ኤልሳቤጥ ቅድስት ማሪያምን “የጌታዬ እናት” ብላ ጠራቻት።

የሥላሴ መገለጥ በጥምቀት

ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዮሐንስ ጥምቀት ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረደ። ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስ በአካል መልክ እንደ እርግብ አምሳል በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም የመጣ የእግዚአብሔር አብ ድምጽ ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው’ እርሱን ስሙት አለ። ሥላሴ በአካል ሦስት መሆኑን በሰዎች ሁሉ ፊት ገለጠ።

የክርስቶስ አምላክነት

ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ኢየሱስን ባየው ጊዜ ያቀረበው አምልኮ የክርስቶስን አምላክነት በግልጽ ያሳያል።

“ቶማስም መልሶ፦ ጌታዬና አምላኬ አለው።” — ዮሐንስ 20:28

ኢየሱስ ይህንን የአምልኮ አገላለጽ አልተቃወመም፤ ይልቁንም ተቀብሎታል። ይህም እርሱ በእውነት አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።

የጌታችን ትእዛዝ

“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” — ማቴዎስ 28፥18-20

እዚህ ላይ ኢየሱስ "በስሞች" (ብዙ ቁጥር) ፋንታ "በስም" (አንድ ቁጥር) መጠቀሙ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አንድነት ያመለክታል። ሦስቱም አንድ መለኮታዊ ስምና ሥልጣን አላቸው።

የሐዋርያት ትምህርት

ሐዋርያት እግዚአብሔር አብ አምላክ ስለመሆኑ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለመሆኑ እና መንፈስ ቅዱስም አምላክ ስለመሆኑ በግልጽ አስተማሩ፤ ነገር ግን ሦስት አማልክት ሳይሆኑ አንድ አምላክ መሆኑን አጽንተዋል።

  • ስለ አብ፦ “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን...” (1ኛ ቆሮንቶስ 8፥6)
  • ስለ ወልድ፦ “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።” (1ኛ ዮሐንስ 5፥20)
  • ስለ መንፈስ ቅዱስ፦ “ጴጥሮስም፦ ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልል ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ... እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 5፥3-4)

የሐዋርያት ቡራኬ

ሐዋርያው ጳውሎስ በብዙ መልእክቶቹ መጨረሻ ላይ የሚጠቀመው ቡራኬ የሥላሴን አካላት በእኩል ደረጃ ያስቀምጣል።

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔርም ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።” — 2ኛ ቆሮንቶስ 13:14

ይህ ጥቅስ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በመለኮታዊ ሥራቸውና በባሕርያቸው አንድ መሆናቸውን ያሳያል።

ሐዋርያት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአካል የተለያዩ መሆናቸውንም አስተምረዋል። ጌታ ኢየሱስ ራሱ “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” (ዮሐ 14፥16) ብሏል። አብ ወልድ አይደለም፤ ወልድም መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ ነገር ግን ሦስቱም አንድ አምላክ ናቸው።

የቀደመችው ቤተክርስቲያን አባቶች ምስክርነት

ከሐዋርያት ቀጥለው የመጡት የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህንን እውነት ጠብቀው አስተላልፈዋል።

ቅዱስ አግናጢዮስ (30-110 ዓ.ም.)

“ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመናት መጀመሪያ በፊት ከአብ ጋር የነበረው በመጨረሻውም ዘመን የተገለጠው… እርሱ ከጥንት ዘመን በፊት ከአብ የተወለደ አንድያ ልጅ የሆነው እግዚአብሔር ቃል ነበር። እናም ለዘለአለም ያው ሆኖ ይኖራል ‘ለመንግስቱም መጨረሻ የለውም’ ይላል ነቢዩ ዳንኤል።”

ቅዱስ ፖሊካርፕ (የዮሐንስ ደቀመዝሙር)

“ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ሆይ…ዘላለማዊና ሰማያዊ በሆነው ሊቀ ካህናት በምትወደውና ባከበርኸው ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአንተና ለእርሱም እንዲሁም ለመንፈስ ቅዱስ ለአሁንም ሆነ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን”

ዲዳኬ (የ12ቱ ሐዋርያት ትምህርት)

“...በሚፈስ ውሃ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቅ...”

ተርቱሊያን (160-215 ዓ.ም.)

“አብና ወልድ ሁለት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ደግሞ ሦስት መሆናቸውን እንገልጻለን... ሦስት ናቸው። ነገር ግን በባሕርይ ሳይሆን በገጽ፤ በኀይል ሳይሆን ነገር ግን በዐይነት:: በባሕርይና (substance) በኀይል አንድ ናቸው፤ ምክንያቱም አንድ አምላክ ብቻ ስላለና ይህም ባሕርይ ገጽና ዐይነት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ዙሪያ ያለ በመሆኑ።”