መጽሐፍ ቅዱስ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ እግዚአብሔር የድነት ታሪኩን ለሰው ልጆች የገለጠበት፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና እስትንፋስ ሙሉ በሙሉ ተጥብቆ የተጻፈ ፍጹም ቃሉ መሆኑን እናምናለን። ይህ ቃል በዋና ቅጂዎቹ ስሕተት የሌለበት ፣ የማይሻር ፣ እንዲሁም ለእምነትና ለሕይወት ልምምድ የመጨረሻው የበላይ ባለሥልጣን ነው።
"ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።" (2 ጴጥ. 1:21)።
"የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም እንዲሆን ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ እንዲሆን፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።" (2 ጢሞ. 3:16)።
የቃሉን አፈታት በተመለከተ፣ ጤናማ የሆነ ታሪካዊና ሰዋሰዋዊ የአተረጓጎም ሥርዓትን እንከተላለን። በዚህም መሠረት የዘፍጥረት የፍጥረት ታሪክ ምሳሌያዊ ሳይሆን እውነተኛና ታሪካዊ ክስተት መሆኑን፣ እንዲሁም አዳምና ሔዋን የሰው ዘር ሁሉ ታሪካዊ ቀዳማውያን ወላጆች መሆናቸውን እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያናዊ አስተምህሮ ብቸኛ ምንጭና ፍጹም መለኪያ ነው።
እግዚአብሔር
እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ጀማሪና ደጋፊ፣ በራሱ የሚኖር ፣ የማይለወጥ ፣ ብቸኛና ሕያው አምላክ መሆኑን እናምናለን። እርሱ ጊዜንና ታሪክን የሚገዛ፣ ከፍጥረት ሁሉ በላይ የሆነ ልዑል አምላክ ነው። "ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርና ዓለም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።" (መዝ. 90:2)።
መለኮታዊ ባሕርዩም ፍጹም ቅዱስ (ራዕ. 4:8)፣ ዘላለማዊ (ኢሳ. 57:15)፣ እና ማለቂያ የሌለው ነው። እርሱ ሁሉን ቻይ "እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔር የሥጋ ሁሉ አምላክ ነኝ፤ የሚሳነኝ ነገር አለን?" (ኤር. 32:17, 27)፣ በሁሉ ሥፍራ የሚገኝ (መዝ. 139:7)፣ እና የሰውን ልብና የታሪክን ፍጻሜ የሚያውቅ ሁሉን አዋቂ (1 ዮሐ. 3:20) ነው።
እግዚአብሔር በመለኮታዊ ማንነቱ መንፈስ (ዮሐ. 4:24)፣ ፍቅር (1 ዮሐ. 4:8, 16)፣ ብርሃን (1 ዮሐ. 1:5) እና እውነት (መዝ. 117:2) ነው። የድነት ታሪክ ታላቅ መሐንዲስ እንደመሆኑ መጠን፣ እርሱ ብቻውን በፍጥረት ሁሉ ሊመለክ (ዘፍ. 24:26)፣ ሊገለገል (ማቴ. 4:10)፣ እና ወንጌሉ በዓለም ሁሉ ሊታወጅ (የሐዋ. 1:8) የሚገባው የታሪክ ሁሉ ጌታ ነው።
ሥላሴ
በእግዚአብሔር ሥሉስ አሐዳዊነት እናምናለን። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ፣ በኅልውናው እና በዘላለማዊነቱ አንድ አምላክ ሲሆን፣ ይህ አንድ መለኮታዊ ባሕርይ በአብ፣ በወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ)፣ እና በመንፈስ ቅዱስ ሦስት የተለዩ፣ ነገር ግን የማይነጣጠሉ ዘላለማዊ አካላት ይገለጣል። ሦስቱም አካላት በሥልጣን፣ በክብርና በመለኮታዊ ሙላት ፍጹም እኩል ናቸው። ይህ ማለት ሦስት አማልክት አሉ ማለት ሳይሆን፣ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ለዘላለም ይኖራል ማለት ነው። እንዲሁም አንድ አካል በተለያዩ ዘመናት ሦስት ዓይነት የሥራ ድርሻዎችን፣ ሥልጣኖችን ወይም ቅርጾችን ይዞ ተገለጠ ማለት አይደለም።
"እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም መጨረሻው ነኝ፥ ከእኔም በቀር አምላክ የለም።" (ኢሳ. 44:6)።
"እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር..." (ዘፍ. 1:26-27)።
"እነሆም፥ ድምፅ ከሰማይ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።" (ማቴ. 3:17)።
"የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔርም ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።" (2 ቆሮ. 13:14)።
ታሪካዊ ማረጋገጫ፡ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎችና ኦርቶዶክሳዊ አቋም
የፕሮቴስታንት ተሐድሶ የካቶሊክን የድነት ትምህርት በጥብቅ ቢቃወምም፣ ስለ እግዚአብሔር ማንነት እና ስለ ሥላሴ ያለውን የጥንታዊቷን ቤተ ክርስቲያን ፣ በተለይም የመጀመሪያዎቹን አራት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች፣ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ይቀበላል። በኒቅያ (325 ዓ.ም) እና በቁስጥንጥንያ (381 ዓ.ም) ጉባኤዎች፣ እንዲሁም በአትናቴዎስ የሃይማኖት መግለጫ በተብራራው መሠረት፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር በመለኮታዊ ባሕርይ አንድ መሆናቸውን እናምናለን። ጆን ካልቪን እና ማርቲን ሉተርን የመሳሰሉ የተሐድሶ አባቶች፣ ክርስቶስ ፍጡር ነው የሚለውን የአርዮስን ክህደት ፣ እንዲሁም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የአንድ አካል ሦስት የተለያዩ መገለጫዎች ብቻ ናቸው የሚለውን የሰባልዮስን ስሕተት አጥብቀው በማውገዝ፣ የሥላሴ ትምህርት በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚመነጭ የማይናወጥ የክርስትና ማዕዘን መሆኑን ደንግገዋል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ዓለም አቀፉ የጴንጤቆስጤ እና የወንጌላውያን ንቅናቄም ይህንኑ ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሥላሴ ትምህርት የክርስትና እምነት የደም ሥር አድርጎ አጥብቆ ይዟል። ምንም እንኳን "ኢየሱስ ብቻ" (Oneness Pentecostalism) የሚባሉና ከታሪካዊው ክርስትና ያፈነገጡ ጥቂት የኑፋቄ ቡድኖች ቢነሱም፣ ጤናማውና ዋናው የወንጌላውያን ንቅናቄ ግን አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በአንድነት የሚያምንና የሚያመልክ ነው።