የህይወት ቃል ህብረት
Doctrine of Revelation

መገለጥ

"ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።" (ማቴዎስ 11፥27) ፤ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚቻለው እርሱ ራሱን በገለጠበት መመዘኛና አቅም ልክ ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ የሰውን ልጅ ምሁራዊ ጥረትና ፍልስፍናዊ ምርምር ወደ ኋላ የሚተው፣ ከሰማያት ሰማያት በሉዓላዊ ፈቃድ የፈሰሰ የጸጋ ስጦታ ነው። የሰው ልጅ ውብና ግርማ ሞገስ ያለውን የተፈጥሮ ሥነ-ፍጥረት በመመልከት፣ የፈጣሪን ታላቅነትና ጥበብ በከፊል ማድነቅ ቢችልም (ሮሜ 1፡20)፤ በኃጢአት በጨለመውና በወደቀው አእምሮው (ኤፌ. 4፡18) ወደ ዘላለም ሕይወትና ወደ እውነተኛው የድነት ብርሃን የሚያደርሰውን አዳኝ እውነት በራሱ ጥረት ፈጽሞ ሊደርስበት አይችልም። እግዚአብሔር በምሕረቱና በዘላለም ፍቅሩ ወደ እኛ ካልመጣ፣ ራሱንም ካልገለጠልን በቀር፣ እኛ የቱንም ያህል በምድራዊ ጥበብ ብንመራመር ከቶውንም ልናገኘው አንችልም (ኢዮብ 11፡7)። ስለዚህ መገለጥ ማለት፣ የሰው ልጅ በእውቀቱ ተመራምሮ የደረሰበት የፍልስፍና ግኝት ሳይሆን፤ ታላቁ፣ ቅዱሱና የማይደረስበት አምላክ በፍቅር ሲጠራን የምንሰማበትና የምንድንበት ሕያው መለኮታዊ ድምፅ ነው። እኛ በምናባችን ጣዖት እንደሚቀርጽ ሰው አምላክን በአእምሯችን አንፈጥረውም፤ ይልቁንም እርሱ በጸጋው ብርሃን ጠርቶ፣ ከጨለማ አውጥቶ የራሱ ልጆች ያደርገናል።

በክርስቲያናዊ ሕይወታችን የምንገነባው የነገረ-መለኮት ሕንጻና የእምነት ግንብ ሁሉ የሚቆመው፣ "እግዚአብሔር ተናግሯል!" በሚለው በዚህ የማይናወጥ የመገለጥ ዓለት ላይ ነው። ስለ አምላካችን ቅድስና፣ ነፍሳችንን ከሲኦል ፍርድ ስለዋጀበት የጎልጎታ የማዳን ሥራ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ውበት፣ ወይም ስለ መጨረሻው ዘመን የክብር ተስፋ ከመናገራችን በፊት፣ "ይህን ሁሉ ድንቅ የሰማይ ምስጢር ከየት አወቅን?" ብለን ብንጠይቅ፣ ምላሻችን አንድና አንድ ብቻ ነው፦ "እግዚአብሔር ራሱ ስለ ራሱ በቃሉ ነግሮናል!" ይህ እውነት ነፍሳችንን ከሰው ልጅ ተለዋዋጭ ስሜት፣ ከዘመኑ የፍልስፍና ንፋስ እና ከግላዊ ግምት ነፃ አውጥቶ በጽኑ መልሕቅ ያስራታል። ስለ እግዚአብሔር ያለን እውቀት እውነተኛ፣ ሕያውና አዳኝ የሚሆነው፣ በሰዎች የተለዋዋጭ ጥበብ ላይ ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉም ፈጽሞ በማያልፈውና ስሕተት አልባ በሆነው በሕያው ቃሉ ላይ ሲመሠረት ብቻ ነው።

ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔርን ራሱን ዝቅ ማድረግ በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ስናስተውል፣ የልባችን ትዕቢት ይሰበራል፤ ነፍሳችንም በጥልቅ ትሕትናና በማያልቅ የአምልኮ ምስጋና ትሞላለች። ትሕትናችን የሚመነጨው፣ ያገኘነው የብርሃን እውቀት የራሳችን የብቃት፣ የጽድቅ ወይም የምርምር ውጤት ሳይሆን የነጻ ጸጋው ስጦታ መሆኑን ከማወቅ ነው፤ ምስጋናችን ደግሞ፣ ከሰማያት ሰማያት በላይ ከፍ ያለው፣ ኪሩቤልና ሱራፌል በፊቱ የሚንቀጠቀጡለት ቅዱሱ አምላካችን፣ አፈርና ትቢያ ለሆንነው ለእኛ ሲል ራሱን ዝቅ አድርጎ እኛ ልንረዳው በምንችለው የሰውኛ ቋንቋ ስለተናገረን ነው። ከኤደን ገነት የ"አዳም ሆይ ወዴት ነህ?" ድምፅ ጀምሮ እስከ ራእይ መጽሐፍ የ"አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና" ፍጻሜ ድረስ የምናየው፣ ይህንኑ የእግዚአብሔርን ዝቅ ማለትና የጠፋውን የሰው ልጅ ለመፈለግ በፍቅር ወደ ምድር መምጣት ነው። ይህ ወደር የሌለው መለኮታዊ ፍቅር፣ ዘላለማዊው ቃል ሥጋ በሆነውና ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ መካከል ባደረው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል (ዮሐ. 1፡14) በሚታይ፣ በሚዳሰስና በሚያድን ሁኔታ ፍጹም ሆኖ ተገለጠልን።

አሁን ደግሞ በዚህ መንፈሳዊና ጥልቅ የነገረ-መለኮት ጉዞ ውስጥ፣ ይህንን ታላቅ የመገለጥ ታሪክ በስድስት አበይት እርከኖች አብረን እንመለከተዋለን። በመጀመሪያ የሰው ልጅን ሁለንተናዊ ውድቀትና የኃጢአት መጋረጃ ስናይ፣ የመገለጥን ፍጹም ወሳኝነት በጥልቀት እንረዳለን፤ አጠቃላይ ፍጥረትንና ሕሊናን ስንቃኝ፣ የአምላክን የማይካድ የጣት አሻራ እናያለን፤ ከዚያም ወደ ልዩ መገለጥ ስንሸጋገር፣ የመገለጥ ሁሉ ጫፍ፣ ማዕከልና ፍጻሜ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ፊት ለፊት እንገናኛለን። ቅዱሳት መጻሕፍትንና የቃሉን እስትንፋስነት (Inspiration) የሠራውን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ስንመረምር እውነቱ እንዴት ያለ ስሕተት እንደተጠበቀልን እናያለን፤ እንዲሁም የእምነትን እርምጃ፣ እግዚአብሔር ራሱን ቀስ-በቀስ የገለጠበትን መለኮታዊ ጥበብ፣ እና የመገለጥን የባሕልና የመጨረሻ ዘመን ፋይዳ በጥልቀት እንቃኛለን።

✦ ✧ ✦

የጥናቱ ክፍሎች

ለጥልቅ ንባብ አንዱን ክፍል ይጫኑ

፩

የመገለጥ መሠረትና ባሕርይ

Foundation & Nature

የሰው ልጅ ህልውናዊ ውስንነት፣ ኃጢአተኝነት፣ የፈጣሪና ፍጡር ርቀት፣ መገለጥ ግላዊና ጸጋዊ መሆኑ።

፪

አጠቃላይ መገለጥ

General Revelation

ፍጥረት፣ ሕሊና፣ ጥበቃ — ዓላማውና ድነታዊ ውስንነቱ።

፫

ልዩ መገለጥና ክርስቶስ

Special Revelation & Christ

ቴዎፋኒ፣ ራእይ፣ ትንቢት፣ ተአምራት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፤ በክርስቶስ የመገለጥ ሙላት።

፬

ቅዱሳት መጻሕፍትና መንፈስ ቅዱስ

Scripture & the Spirit

መነሳሳት፣ ሁለትዮሽ ጸሐፊነት፣ ቀኖና፣ ግልጽነት፣ አብርሆት።

፭

እምነት፣ ደረጃ-በደረጃ መገለጥና ትውፊት

Faith, Progressive Revelation & Tradition

እምነት ለመገለጥ የሚሰጥ ምላሽ፣ ከዘፍጥረት እስከ ክርስቶስ ያለው እድገት፣ ትውፊት።

፮

ባሕልና የመጨረሻው ዘመን

Culture & Eschatology

የኒበር አምስት ሞዴሎች፣ ሁኔታዊ መግለጫ፣ "አሁን የተጀመረ ገና ያልተጠናቀቀ" ውጥረት።

የተገለጠውን ቃል በትሕትና መቀበል

ወደ ኋላ ተመልሰን ስንመለከት፣ በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት የተገለጠልን ታላቁ እውነት አንድ ወጥ የሆነ፣ ሉዓላዊና መለኮታዊ ትረካ ያሳየናል ። ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ዘላለማዊ ፍጻሜው ድረስ፣ ተናጋሪውም፣ ፈላጊውም፣ ራሱን ገባሪውም ራሱ ሕያው አምላክ ነው። እኛ የጠፋውን ፈጣሪ በራሳችን ሰዋዊ ፍልስፍና የፈለግን ፈላጊዎች አይደለንም፤ ይልቁንም በኃጢአት ጥልቀትና በጨለማ ውስጥ የጠፋውን ሰው በዘላለማዊ ፍቅሩ የፈለገው እርሱ ራሱ ነው። እኛ በምርምራችን እውነትን አግኚዎች አይደለንም፤ እርሱ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሕያው ቃሉ ራሱን የገለጠው ብቸኛው ጌታ ነው። ይህ ሰማያዊ እውነት የተማርነውንና የዳሰስነውን የትምህርተ-መገለጥ ሐሳብ ሁሉ ወደ አንድ ማዕከል ይመልሰናል፦ በሰው ልጅ የፍጡርነት ውስንነት እና በውድቀት ባመጣው ሁለንተናዊ ኃጢአተኝነት ምክንያት መገለጥ ለእኛ የሞትና የሕይወት ጉዳይ (ግድ አስፈላጊ) ሆነ፤ እግዚአብሔርም በፍጥረት ግርማ፣ በውስጣዊ ሕሊና እና በዕለታዊ ጥበቃው አማካኝነት ራሱን ለሁሉም ፍጡር በአጠቃላይ አሳወቀ፤ በቴዎፋኒ፣ በነቢያት አዋጆች፣ በተአምራት ምልክቶች እና በመጨረሻም በዘላለማዊ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዌ አማካኝነት ልዩ፣ ሕያውና አዳኝ የሆነውን የቤዛነት ፈቃዱን ገለጠ፤ ያንን መለኮታዊ መገለጥ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያለ አንዳች ስህተት ጠብቆ አኖረልን፤ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው አሠራርና አብርሆት ደግሞ ያንን የተጻፈ ቃል በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ያበራዋል፤ ይህ መገለጥ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ደረጃ በደረጃ እያደገ፣ ማዕከሉ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እየመራ ይሄጣል፤ በመጨረሻም በምድራዊ ሕይወታችንና በዘመናችን ውስጥ ኖረን፣ በክብር ወደ ሙላቱ ወደሚመጣው የመንግሥት ተስፋ በጉጉትና በተስፋ እንድንጠባበቅ ያደርገናል።

ይህ ጥልቅ ትምህርት ለክርስቲያናዊ ሕይወታችንና ለነፍሳችን የሚሰጠው ጥቅም ከደረቅ ንድፈ-ሐሳብ ወሰን እጅግ የላቀና ሕይወት ሰጪ ነው። በመጀመሪያ፣ ማናችንንም ወደ ጥልቅ ትሕትና ይመራናል፤ ምክንያቱም ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ማዳኑና ስለ መንግሥቱ የምናውቀው እውቀት ሁሉ ከራሳችን አእምሯዊ ብልህነት፣ ጥረት ወይም የትምህርት ብቃት የመጣ ሳይሆን፣ ፈጽሞ ሊገባን በማይገባ ቸርነት የተሰጠ ንጹህ የጸጋ ስጦታ መሆኑን ስለምንገነዘብ ነው። ሁለተኛ፣ የማይናወጥ እርግጠኝነትን ይሰጠናል፤ ምክንያቱም እምነታችን በተለዋዋጭ ስሜታችን፣ በወቅታዊ ሁኔታዎች ወይም በሰዋዊ ግምት ላይ ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር ቢለወጡም በማይለወጠው፣ በሰፈረው፣ በተጠበቀውና በሕያው እግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ መሆኑን በውል ስለምናውቅ ነው። ሦስተኛ፣ በልባችን ውስጥ የማይለቅ ምስጋናን ያፈልቃል፤ ምክንያቱም ከሰማያት ሰማያት በላይ ከፍ ያለው ወሰን-የለሽ አምላክ፣ አፈርና ትቢያ ለሆንነው ለእኛ ሲል ራሱን ዝቅ አድርጎ ፣ በመጨረሻም ሥጋ ለብሶ በመካከላችን በመኖሩ፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለእኛ ለማሳወቅና ከእርሱ ጋር እንድንታረቅ በመምረጡ ነው። አራተኛ፣ ለታላቁ ተልእኮ ሕያው ቅናትንና ተልእኮን ያነሳሳናል፤ ምክንያቱም ይህ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበልነው ውድ መገለጥ ለራሳችን ብቻ ተሰጥቶን በውስጣችን እንድንዘጋበት ሳይሆን፣ በጨለማ ለሚገኙት የዓለም ዳርቻዎች ሁሉ በታማኝነትና በድፍረት ልናካፍለው የሚገባን የሕይወት እንጀራ መሆኑን ስለምንረዳ ነው።

ውድ አንባቢ፣ ይህንን መንፈሳዊ የጥናት ጉዞ ስትዘጋ፣ በልብህ ፊት ሊቆም የሚገባው ብቸኛና አጣዳፊ ጥያቄ ይህ ነው፦ ዛሬ ለተገለጠልህና በሰማያዊ ኃይል ለሚጮኸው ለእግዚአብሔር ቃል በእምነት፣ በስብራትና በታዛዥነት ምላሽ ትሰጣለህን? የተገለጠው የሕይወት ቃል በደብተርህ ውስጥ የሚቀመጥ ደረቅ መረጃ ወይም በአእምሮህ ማኅደር ብቻ የሚዘጋ የቲዎሪ ትምህርት ሆኖ እንዲቀር አትፍቀድለት፤ ይልቁንም ሕያው ቃሉ ልብህን እንዲያርስ፣ ኑሮህንና ጠባይህን እንዲቀርጽ፣ አእምሮህን እንዲያድስ፣ እና የመጨረሻውን የዘላለም ተስፋህን እንዲያጽናፈው ለፈጣሪህ እጅ ስጥ። ሐዋርያው በዕብራውያን መልእክት እንዳስጠነቀቀን፣ እግዚአብሔር በነቢያት፣ በልጁ በክርስቶስ፣ በተጻፈው ቅዱስ ቃል፣ እና አሁንም በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ድምፅ አማካኝነት ዛሬም በልባችን ይናገራል። "እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል፦ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ በምድረ በዳ ፈተና ቀን እንዳደረጋችሁት ልባችሁን አታደንድኑ" (ዕብ. 3፥7-8)። አዎን፣ የፈጣሪን ጥልቅ ምሥጢራት ሁሉ ማወቅ ባይቻለንም፣ "ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን ለእኛና ለልጆቻችን ነው" (ዘዳግም 29፥29)። ይህንን በጸጋ የተገለጠውን ታላቅ መለኮታዊ እውነት በትሕትና ተቀብለን፣ በማያልቅ ምስጋና ተሞልተን፣ የማይናወጥ ተስፋ ጸንተን፣ ያንን የክብር ቀን ፊት ለፊት በክብር የምናየው ቀን በጉጉትና በንቃት እንጠባበቅ። ክብርና ውዳሴ ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን! አሜን።