ክርስቲያንና ባህል
(ባህላዊ አመቻማችነት)
ዘላለም መንግስቱ
የክርስትና ግብ ባህል ቀያሪነት አይደለም። ከርስቲያን በባህል መጠለፍም የለበትም፡፡ የክርስትና ግብ አዲስ ፍጥረትነት ነው። አዲስ ፍጥረት የሆነ ሰው ደግሞ ውስጡ ተለውጦ ውጪውም ይለወጣል፡፡
ማናችንም ተወንደን ያደግንበት ማኅበረ ሰብ አለን። ያ ማኅበረ ሰብ ደግሞ ባህል አለው። ባህልን ስናስብ የሕይወታችንና የኑሯችን ድርና ማግ ሆነው የሚመጡልን ብዙ ምስሎች አሉ። ሠርግ፥ ትዳር፥ ለቅሶ፥ ቀብር፥ ወሊድ፥ ዐውደ ዓመት፥ ድግሶች፥ አመጋገብ፥ ጉርምስና፥ ኩርድና፥ ቤተ ዘመድ፥ ሠላምታ፥ ጥየቃ፥ አለባበስ፥ የወንጀል ምርመራ፥ አውጫጭኝ፥ ብቀላ፥ ሽለላ፥ ቀረርቶ፥ ዘፈን፥ ሽምግልና፥ እርቅ፥ ካሳ፥ የአረጋውያን ክብር፥ የመሪዎች አክብሮት፥ ዝምድና፥ ጋብቻ፥ አምቻ፥ ጉዲፈቻ፥ አበ ልጅነት፥ አምልኮ፥ የተክለ ሰውነት አያያዝ፥ ወዘተ፥ ወዘተ። ከአምልኮ ጋር የሚቆራኘው የሃይማኖት ጉዳይ የተለየ ቢሆንም በአንዳንድ ባህሎች ባህሉና ሃይማኖቱ ተደባልቀው ይገኛሉ፡፡ ወይ ባህሉ ሃይማኖታዊ ባህል፥ ወይም ሃይማኖቱ ባህላዊ ሃይማኖት ይሆናሉ፡፡ እዚህ አንዱን ከሌላው መለየት ይከብዳል። ቢሆንም በዚህ ጉዳም ማይማን መሆን የለብንም።
ባህል ሰፊ ነገሮችን በውስጡ ይይዛል። እዚህ ላይ ባህል ምንድር ነው? ብለን መጠየቅ አለብን። ባህል ምንድር ነው? ባህልን በቀላሉ መተርጎም ያዳግታል። የሚያዳግተው የብዙ ነገሮች ቅይጥና ድርና ማግ ሥሪት ስለሆነ ነው። ክርስቲያንና ዘፈን በሚለው ትምህርት ውስጥ ስለ ዘፈንና ባህል ግንኙነት ሳካፍል ስለ ባህል ያልኩትን እዚህም እለዋለሁ፡፡ ይህኛው ስለራሱ ስለ ባህል የማካፍለው ነውና እዚህ በትንሹ ሰፋ አደርገዋለሁ፡፡
ባህል ተቀባይነትን ያገኘ የአንድ ሕዝብ ወይም የአንድ የሕዝብ ክፍል የጋራ መታወቂያ ወይም መለያ የሆነ ልማድ፥ ደንብ፥ ወግ፥ አመለካከት ነው። ባህል ሕዝባዊ ወይም ማኅበራዊ መስተጋብር ነው። አንድን የሕዝብ ክፍል ማኅበረ ሰብ ከሌላ የሕዝብ ክፍል ለይቶ ማወቂያ ወይም መታወቂያም ነው፡፡ ባህል ከማኅበረ ሰቡ የቀደመ ታሪክ የተወረሰ፥ የአሁን ማንነቱን በሚገልጡ ብዙ ገጽታዎች የዳበረና ተጠላልፎ፥ ተገማምዶ የተያያዘ ነው። ይህ የአንድ ማህበረ ሰብ ሕዝባዊ ባህል ወይም ዋና ባህል ነው። Mainstream culture ይባላል።
ባህል በቋንቋ፥ በስነ ቃል፥ በስነ ጥበቦች፥ በተለያዩ ድርጊቶች፥ አምልኮዎችና ሥርዓቶች ከአንዱ የዚያ ሕዝብ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ይተላለፋል። አንድ ባህል ወይም የትኛውም ባህል የማይሰረዝ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ የተጻፈና ለሁሉም ሰዎች እና ለሁልጊዜ ሊሆን የተገባው ሕግ አይደለም። ባህል ይወለዳል፥ ያድጋል፣ ይቀየራል፤ ይለወጣል፤ ይሟሟል፤ ይታወሳል፤ ይዘነጋል። ባህል ይወርሳል፤ ይወረሳል፤ ከሌላ ባህል ይወስዳል፤ ለሌላ ባህል ይሰጣል። በዚያው በአንዱ ማኅበረ ሰብ ውስጥም እንኳ በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ፥ ወይም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር የሚለዋወጡ ባህላዊ እሴቶች ይኖራሉ፡፡
ብዙ ሕዝብና ማኅበረ ሰቦች ባሉበት እንደኛ ባለ አገር በቁጥርም በዓይነትም ብዙ የሆኑ ባህሎች እናገኛለን። አንድ ሰው በአንድ ነጠላ ባህል ውስጥ ወይም ከአንድ ባህል በላይ የሆኑ ባህሎች ውስጥ ሊያድግና ሊኖር ይችላል። ባህሎች ከአስተዳደጋችን ጋር የተጣበቁ ስለሆኑ በደስታ ነው የምናስባቸው፡፡ አንዳንድ ባህሎች መልካም ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ጎጂ ናቸው፡፡ ያደግንባቸው ባህሎች ስለሆኑ ጎጂዎቹንም እንደ ጎጂ አናስባቸውም፤ እንደ ጎጂ አንቀበላቸውም። ለምሳሌ፥ የሴቶች ግርዛት ጎጂ ባህል ነው፡፡ ይህንን በማያውቁት ዘንድ እንዲያውም ወንጀል ነው፡፡ ያደግንበት ባህል ከሆነ ግን ጎጂ አድርገን አንቀበለውም። ብዝሐ ጋብቻ በብዙ አገሮች ነውርና ሕገ ወጥነት ነው፤ በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ ወንጀል ነው። ባደግንበት ባህል የተለመደ ከሆነ እንኳን ወንጀል፥ ነውርም አይመስለንም። ደም መመለስ ወይም ብቀላም እንደዚያው፡፡ ሌሎችም ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡
ከባህል ምንነት ጋር ሦስት ቃላትን እንይ። ዋና ባህል (mainstream culture የሚባለውን ተመልክተናል። ሦስቱ ንዑስ ባህል፥ አጸፋ ባህል እና ትውፊት ናቸው፡፡
1. ንዑስ ባህል
ንዑስ ባህል ወይም ስንቅር ባህልም ይባላል፤ (subculture ይሉታል።) ይህ በአንድ ሕዝብ ባህል (mainstream culture) ውስጥ የሚገኝና ከባህሉ ገዢ አቋም በመጠኑ ያፈነገጠ፥ ታግሰውት፥ ችለውት የሚኖሩት አናሳ ባህል ነው። በአለባበስ፥ በአነጋገር ዘዬ፥ በሰውነት አያያዝ፥ በጺም እና ጸጉር አስተዳደግ፥ ወዘተ፥ ሊገለጥ ይችላል፡፡
አንድዳንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ባህሎች በእርከን ይለዩና ከፍ ያሉና ዝቅ ያሉ ተብለው ይለያሉ፡፡ ዝቅ ያለው ዝቅ ያለ የሚባለው የሰፊው ሕዝብ ስለሆነና ከፍ ያለው የጥቂት ልሂቃንና ምሑራን ባህል ስለሆነ ነው። ይህ የአነጋገር ዘዬንና አጻጻፍንም ያጣቅሳል (የጥንቱ ግሪክ ክላሲካል ግሪክ እና ኮይኔ ግሪክ እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዘመናችንም High German እና Low German ምሳሌ መሆን ይችላል በቋንቋ ረገድ፡።) የተለያዩ የሕዝብ ክፍሎች በአንድ አገር ሲኖሩ አንዱ ባህል ጎልቶ ወይም ገንኖ ሊወጣም ይችላል፤ ወይም ያቺ አገር የሁሉም ባህል የሚካሄድባት ኅብረ ባህላዊ (multicultural) አገር ልትሆን ትችላለች።
2. አጸፋ ባህል
ይህኛው ደግሞ አፈንጋጭ ባህል ነው። በአንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ አንድ ትውልድ ወይም በአንድ ትውልድ ውስጥ የሚገኝ የተወሰነ ክፍል ባህሉን ሲንቅ፥ ሲረግጥ፥ ሲጥስ፥ አዲስ የራሱን ባህል ሲመሠርት ያ አጸፋ ባህል ወይም አፈንጋጭ ባህል ይባላል። በእንግሊዝኛ counterculture ይባላል። በአሜሪካ በ1960ዎቹ በወጣቱ ትውልድ የጀመረው አካሄድ ዓይነቱ ነው። ይህ አካሄድ በ1970ዎቹ ቢደበዝዝም አሻራው እስካሁንም ሳይደበዝዝ ቆይቷል። እነዚያ ወጣቶች፥ ቢትኒክስ፥ ሂፒስ፥ እና ዉድስቶክስ ይባላሉ፡፡ የሮክ ሙዚቃ፥ ጸጉር ማሳደግ፥ ለአለባበስ ግድ የለሽ መሆን፥ በአሜሪካ የተከበሩ ነባር ባህሎችን፥ ማኅበራዊ እሴቶችን መናቅ፥ በቡድን አብሮ በመኖር ነፃ ፍቅር የሚሉትን ወሲባዊ ልቅነትና ግብረ ወጥነት መለማመድ፥ ማሪዋና እና ሌሎችም ሱስ አስያዥ ዕጾችን መውሰድ፥ ሌሎችም ይገኙበታል። ፖለቲካዊ አቋሞችንና መንግሥትንም መናቅና መቃወም አለበት፤ ጦርነትን መቃወም፥ የሴቶች መብትና የሲቪል መብቶች ንቅናቄዎች ላይ ድምጽ ማሰማትና እነዚህን የመሰሉ ቢኖሩም፥ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ የጊዜው ንቅናቄዎች ናቸው እንጂ የአጸፋ ባህሉ ውጤት አይደሉም፡፡ ለአጸፋ ባህሉ ያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ትልቁ አጀንዳቸው አልነበረም። ከፖለቲካ ሌላዎቹ ነገሮች ግን የአጸፋ ባህል መገለጫ ነው።
3. ትውፊትስ
ትውፊት ከባህል ይለያል። ባህል የአንድ የተወሰነ ማኅበረ ሰብ ወይም የአንድ ሕዝብ የአንድ ወቅት ወይም ቀጣይነት ያለው ልማድና ወግ ነው። ትውፊት ደግሞ ከአንድ ትውልድ ወደ ቀጣይ ትውልድ፥ እና ተከታታይ ትውልዶች የሚተላለፍ የአንድ ሕዝብ የባህል፥ የልማድ፥ የሃይማኖት፥ የስነ ቃል፥ ወዘተ፥ ተላላፊ ክምችት፥ ቅርስ፥ ወይም ውርስ ነው። ትውፊት በዘመናት ውስጥ የዳበረና የዳጎሰ ስለሆነ፥ የብዙ ትውልዶች ድምር ውጤትም ስለሆነ፥ በአንድ ትውልድ ውስጥ አንለውጠውም፡፡ ትውፊትን አብዮት አካሂደን አንቀይረውም።
ይህ ባህልን በጠቅላላው መልኩ ስንመለከት ሲሆን፥ ነጥባችን ክርስቲያንና ባህል ነውና ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው አሳብ እንምጣ። ወደ ክርስትና ስንመጣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ባህል ሙሉ በሙሉም ባይሆን በአብዛኛው የአይሁድ ባህል ነው። አይሁድ ሕግን የተቀበሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብም ናቸውና፥ ሕዝብ ስለሆኑ ባህልም አላቸው፡፡ ይኑራቸው እንጂ ታዲያ፥ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይጻፉም እንጂ፥ ይህ ባህል ንጥር እና ንጹሕ፥ ወይም የሁሉም ሊሆን የተገባው ባህል ነው ማለት አይደለም፡፡ የአይሁድ ባህል፥ እንደ ሌላው ባህል ሁሉ ነው።
የአይሁድ ባህል ራሱም ንጥር የአይሁድ ባህል አይደለም፡፡ አይሁድ ገና ሕዝብ ሳይሆኑ ነው ወደ ግብጽ የገቡት። ወደ ግብጽ ሲገቡ ቁጥራቸው አንድ መቶም አይሞላም ነበር። ከዚያ በፊት ከአብርሃም እስከ ያዕቆብ ድረስ ያለው ሦስት ትውልድ ከከለዳውያን ዑር ባህል፥ ከሁለት ወንዞች መሐል ወይም ከመስጴጦምያ ባህል፥ እና የተስፋዋ ምድር ከተባለችው የከነዓናውያን አገር ባህል ጋር ትከሻ ለትከሻ የተጋፋ ብቻ ሳይሆን የተቀያየጠም ባህል ነው። ኋላ የግብጽ ሲጨመርበት የአራት ሕዝብ ባህል ቅይጥ ነበር ማለት ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕግ ወይም ትምህርት እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባህል የሚባል ነገር የለም፡፡
አይሁድ ሕዝብ የሆኑት እነዚህን ባህላዊ ዳራዎች ይዘው በግብጽ ውስጥ ነውና የግብጻውያንን ባህልም ሸምተዋል። በእርግጥ ቀድሞ ከብት ወይም እንስሳ አርቢዎች ስለሆኑና አርብቶ አደሮች ደግሞ በግብጻውያን ዘንድ የተጠየፉ ስለሆኑ ለብቻቸው ለምለም በሆነው በጌሤም ኖረዋል። በዚህ ተለይቶ መቆየት ባህላቸው የተጠበቀላቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ ባሪያዎች ከሆኑ በኋላ ያ ባህል የተጠበቀ ነበረ ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ የተቀያየጠ ባህል ማዕቀፍ ውስጥ እያሉ ነው አርነት የወጡትና ሕጉ የተሰጠው፡፡
ሕጉ ባህል አይደለም፡፡ ሕጉ ባህል ዘለልም፥ ድንበር ዘለልም፥ ዘመን ዘለልም ነው፡፡ ኪዳኑ እንደ ኪዳን ከአንድ ሕዝብ፥ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር የተገባ ቢሆንም፥ ኪዳኑ በአዲስ ኪዳን እስካልተተካ ድረስ በዚያ ሕዝብ ላይ ነዋሪ ነው፤ ጉልበታም ነው፡፡ እስካልተተካ ድረስ ነው ያልኩት፡፡ ኪዳኑ ደግሞ ተተክቷል፤ አሮጌው ኪዳን ገና ሕያው ሳለ እግዚአብሔር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ ተናግሮ ነበር፤ "እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤" ኤር. 31፥31።
አዲሱ ኪዳንም በክርስቶስ ደም ተደረገ ወይም ተገባ፤ "ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።" ማቴ. 28፥28። ከመስቀሉ ወዲህ ኪዳኑ ተለውጧል፤ እኛ የአዲሱ ኪዳን ሰዎች ነን፤ "እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።" 2ቆሮ. 3፥6። ሕጉና ኪዳኑ እንዲህ ነው መታየት ያለበት፡፡
የአይሁድ ባህል ግን እንደሌላው ባህል ሁሉ፥ ከላይ ካየነው የመወራረስ ባህርይ ባሻገር ዘመን ዘለልነትና ሁሉን አቀፍነት ባህርይ የለውም። ዘመን ዘለሉ ቃል ግን በባህል ውስጥ ይናኛል ይተገበራል፡፡ ቃሉ ተለዋዋጭ አይደለም፡፡ ቃሉና ባህል ሲጋጩ ቃሉ ባህሉን ይለውጣል እንጂ ባህሉ ቃሉን አይለውጥም። ወደዚህ ነጥብ እመለሳለሁ፡፡
በአዲስ ኪዳን፥ ቤተ ክርስቲያን የተወለደችው በአይሁድ ባህል ውስጥ ቢሆንም ያ ዘመን ግሪካዊና ሮማዊ ባህልና አመለካከት ዓለሙን የገዛበት ዘመን ነበር። ከሮማውያን ቀደም ሲል ግሪካውያን ነበሩ ያንን ዓለም የገዙት። ቤተ ክርስቲያን ተወልዳ ብዙ ሳይቆይ ወደ አሕዛብ ውስጥ ሰርስራ ልትገባ ችላለች። ከሁለቱ፥ ማለት፥ ከአይሁድ እና ከአሕዛብ አንድ የራሱ የሆነ አካል መሥራት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ነበረ። በዘመኑ ለነበሩት ለብዙዎቹ የአሕዛብ ወገኖች ባህላቸው ከሃይማኖታቸውም ጋር የተቆራኘ ነው። ብዙዎቹ የብዝሐ አማልክት እና ጣዖታት አምላኪዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አንድ ጣዖትን ወይም አምላክን ከሌሎቹ ጣዖታት በላይ አድርገው ያመልካሉ እንጂ አንድና አንድ ብቻ አምላክ የሚሉ አልነበሩም። የብዙዎቹ ባህላቸውና ሃይማኖታቸው አብሮ የተለወሰ ነውና አሐዳውያን ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬም በአንዳንድ አሐዳውያን ማኅበረ ሰቦች (unitary society) ሃይማኖትና ባህል የተቆራኙ ናቸው፡፡
የክርስቶስ ወንጌል ነጻ ካወጣቸው በኋላ በአዲስ ኪዳን የምናገኛቸው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ከቀድሞ ልማዳዊ ሃይማኖታቸው ሲላቀቁ ከባህላቸው ውስጥ የቱ ማኅበራዊው፥ የቱ ሃይማኖታዊው መሆኑን ለመለየት ሲቸገሩ ይስተዋላል። የገላትያ፥ የቆላስይስ፥ የሮሜ እና የቆሮንቶስ መልእክቶች እነዚህን ጉዳዮችም ያወሳሉ፡፡ ጴጥሮስ የጻፈላቸው የተበተኑ ወገኖችም ይህ ችግር ነበረባቸው፡፡ ክርስቲያኖች ባህልን በተመለከተ ግልጽ አቋም ሊኖራቸው የተገባ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን በባህል ተደፍጥጣ ባህሉን የምትመስል ወይም በዓለም ቅርጽ ተጨፍልቃ ዓለምን እንድትመስል የተጠራች አካል አይደለችም፡፡ "የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ፡፡" ሮሜ. 12፥2። አማኞች ዓለምን እንዳይመስሉ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ክርስቶስን በመምሰል ዓለምን እንዲለውጡ የተጠሩ ናቸው። "ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልከ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤" ሮሜ 8፥29።
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሕዝቦች ባህል ነበራቸው። ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ ነው የተጻፈው (ከጥቂት ክፍሎች በአራማይስጥ መጽጻፍ በቀር።) አራማይስጥ ከአይሁድ የሰፋ ሕዝብ ቋንቋ ቢሆንም ሁለቱም የአይሁድ ቋንቋዎች ናቸው። አይሁድ ባህልና ወግ አላቸው። ሕጉ ቢጨመርበትም ቀድሞም ወግ ነበራቸው፡፡ አዲስ ኪዳን በግሪካዊና ሮማዊ ባህልና ወግ ውስጥ በግሪክ ቋንቋ ነው የተጻፈው። በሁለቱም ኪዳናት ሕግ ያልሆኑ፥ በሕጉ ውስጥ ያልተጻፉ ልማዶች መኖራቸው አልፎ አልፎ ፍንጥቅ ተደርጎልናል፡፡ ለምሳሌ፥ ሩት. 4፥7-8 ላይ በዘመኑና ከዚያም በፊት የግዢ ማጽኛ እንዲሆን ጫማ አውልቆ መስጠት የተለመደ መሆኑ ተጽፎአል። ይህ በሕጉ ውስጥ የለም፤ ልማድ ግን ነውና በባህላቸው ቦታ ነበረው፡፡ በ1ሳሙ. 2፥13 ሕዝቡ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው ሲቀቀል የካህኑ ሎሌ በሜንጦ ይወስድ ነበር። ልማድ ተብሎአል። በአዲስ ኪዳን ለአገር መሪ በበዓል የወደዱትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረ፤ ማቴ. 27፥15። በዮሐ፣ 19፥40 የአገናነዝ ልማድ የሚባልም ተጠቅሶአል። እነዚህ ልማዶች ወይም የባህል ገጽታዎች ናቸው፡፡
አንድ ማኅበረ ሰብ ሃይማኖት ኖሮትም የባህል ወይም የትውፊት እስረኛ ሊሆን ይችላል። በሃይማኖትና ባህል መስተጋብር ሦስት ዓይነት አቀባበሎች ወይም መቀባበሎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ሕዝብና እንደ ዜጋ፥ አንደኛ፥ ባህላችንን ከማክበራችን የተነሣ ከእምነታችንም የምናስቀድም ልንሆን እንችላለን፤ ሁለተኛ የምናመቻምች እና በባህሉ የምንወሰድ ወይም ሁለቱንም ልናስደስት የምንታገል ልንሆን እንችላለን፤ ወይም ሦስተኛ፥ ባህሉ ለእምነት መገዛት አለበት የምንል ሃይማኖተኞች ልንሆን እንችላለን።
ባህልና እምነት ተቀይጠው ሃይማኖታዊ ባህል ወይም ባህላዊ ሃይማኖት ባለበት ይህ አቀባበል ወይም መቀባበል ችግር አይደለም። ሃይማኖትንም ባህልንም በእኩል ዓይን ለሚያዩ፥ እኩል ክብደት ለሚሰጡ ሰዎች ይህ ችግር የለበትም። ነገር ግን፥ እንደ አማኝ ወይም እንደ ክርስቲያን ደግሞ እምነታችን ከባህላችን ይበልጣልና፥ ይቀድማልና፥ የእምነታችን መመሪያ በባህላችን ላይ መሠልጠን ወይም ባለ ሥልጣን መሆን አለበት፡፡ ብዙዎቹ የባህል መገለጫዎች መልካም ቢሆኑም፥ እነዚህ ሁለቱ ከተጋጩ ትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህ ክፍል የባህልን እና ክርስትናን መስተጋብር በመጠኑ በትነን እንድናይ ያደርገናል። እንደ አገራችን ባለ ብሔረ ሰባዊነት (ወይም የጎሳ ፌዴራላዊነት) የአንድ አገር አስተዳደርና ፍልስፍና ዐቢይ ክፍል ሲሆን የጎሳው ባህል ይገዝፍና፥ የበላይ ይሆንና፥ ሁሉንም ነገር ለመዋጥ ይቃጣዋል። ሃይማኖትንም ጭምር። በአንዳንድ ባህላዊ በዓላት መገኘትና፥ መገኘት ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ መሆንም ግዴታ እስከ መሆን ይደርሳል። ያ በዓል ባህላዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ወይም ከጣዖት አምልኮ ጋር የተቆራኘ ከሆነና ክርስቲያኖች ለመገኘት ባይፈቅዱ ችግር ላይሆንባቸው ይችላል። ነገር ግን መገኘትም መሳተፍም ግዴታው የሚሆንበት ክርስቲያን ሊኖር ይችላል። ያኔ መቆም ያለበትን አቋቋም ማወቅ አለበት። ይህ አምልኮም ሊሆን ስለሚችል በዳን. 3 እንደተጻፉት ወጣቶች የመሰለ የጀርባ አጥንት ያስፈልጋል፡፡
ክርስትና የባህል አብዮትን እንዲያካሂድ መጠበቅም ማሰብም የለብንም። ወንጌል ወደ አይሁድም ሆነ ወደ አሕዛብ ሲገባ በመጀመሪያ ባህልን አልለወጠም። ጌታ የሰጠው ተልእኮ ባህልን የመለወጥ ተልእኮም አልነበረም። ዓለማችን የሚያስፈልጋት የባህል ለውጥ ወይም የባህል አብዮት አይደለም። የዓለማችን ወይም የሰው ልጆች መሠረታዊ ችግር ባህል ሳይሆን ኃጢአት ነው። ችግሩ ባህል ቢሆን ኖሮ መፍትሔው የባህል ቅየራ ሊሆን በተገባም ነበር። ነገር ግን ችግሩ ባህል ሳይሆን ኃጢአት ስለሆነ መፍትሔው ደግሞ አዳኝ ነው። አዳኙም ኢየሱስ ነው፡፡
ወንጌል ውስጥን፥ መንፈስን፥ መንፈሳዊ ማንነትን ነው በመጀመሪያ የሚለውጠው፡፡ ይህ ውስጣዊ ለውጥ ከውስጥ ይጀምርና አድማሱ እየሰፋ ይሄዳል። አካልን ይለውጣል፥ አእምሮን ይለውጣል፤ ስሜትን ይገዛል፥ ይማርካል፤ ቤተ ሰብን ይቀይራል፤ ወደ አኗኗርና አካሄድ ይዘልቃል፤ ወደ ባህልም ይሰርጻል፡፡ ይህ የተለወጠ ማንነት ባህሉን ሊፈትሽና ከቃሉ ጋር ከተጣጣመ ሊቀበለውና አዲሱንና ዋናውን ተልእኮውን ሊያሰርጽበት፤ ካልተጣጣመ ደግሞ ሊገፋውና ሊፋታው፥ ወዲያም ሊለው ይችላል፤ ይገባልም። ባህል በአዲሱ ማንነቱ ላይ በግዴታ ሊጫንበት አይገባም። በአገራችን አንድ ሰው ጌታን ሲቀበል የሚደርስበት አንዱ ስደት ባህሉን መጣሉ ነው። ከሃይማኖታውያኑ ዘንድም እንኳ ከሃይማኖት ይልቅ ስለ ባህላቸው ሲሉ ነው ለመበቀል የሚነሡት፡፡ ስለ ባህላቸው መሆኑን የምናውቀው፥ ከእነዚህ ተበቃዮች አንዳንዶቹ ስለ ሃይማኖታቸው ስለ ራሱ ምንም እውቀትም፥ ደንታም የሌላቸው በመሆናቸው ነው። ስለ ሃይማኖታቸው ማይማን ሆነው ለባህላቸው ግን ተቆርቋሪ ናቸው።
በሁለት አጫጭር መጣጥፎች አንዴ በኢሬቻ በዓል እና አንዴ በመስቀል በዓል ላይ ጽፌአለሁ። እነዚህ ባህላዊም ሃይማኖታዊም በዓላት ናቸው። መስቀል ስሙ አዲስ ኪዳናዊ ቢሆም በዓሉና አከባበሩ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። የአዲስ ኪዳኑ መስቀል የሚሸከሙት የደቀ መዝሙርነት መታወቂያ እንጂ የሚያከብሩት በዓል ሆኖም አያውቅም፡፡ ክርስቲያኖች በነዚህ በዓላት ሲሳተፉ ምን እያደረጉ መሆናቸውን በውል ማወቅ ይኖርባቸዋል። አንዱ የኢሬቻ ጉዳይ ጽሑፌ አንድ ክርስቲያን ለጻፈው መጣጥፍ ምላሽም ነው። ይህን 'ክርስቲያናዊ' መጣጥፍ ኢሬቻን ክርስትና አስነሥቶ (ማስመሣት የሚባል ነገር ከኖረ) ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊያደርገውና ክርስቲያኖችም በሙሉ ልብ እንዲሳተፉበት የሄደበት የትየለሌ ርቀት ነው ምላሽ እንድሰጥበት ያደረገኝ፡፡ ክርስቲያኖች በባህላዊና ሃይማኖታዊ ከባቢዎች ሲገኙና ሲሳተፉ እምነታቸውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋማቸውም መሠሪያ ላይ አጋድመው መሆን ፈጽሞም የለበትም። ክርስትና ባህልን መቀየር ዋና ግቡ ባይሆንም በሂደት ውስጥ በባህል ላይ ተጋቦትን ያሳድራል እንጂ የባህል መርፌ ተወግቶ ልምሻ አይይዘውም፡፡
አንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ሲወጡ የነጮችን ቀንበር አርቀው የጣሉና የተበቀሉ እየመሰላቸው፥ ዘመናዊ እውቀትን ከቀሰሙ በኋላም እንኳ ከቅኝ አገዛዝ ዘመናት በጣም በፊት የነበሩ የቀደሙ ትውልዶችን ልማዶችና ባህሎችን ከመነመኑበትና አንዳንዶቹንም ከሞቱበትም እያወጡ ሲተገብሩና ሲኖሩባቸው ይታያሉ። ክርስትናን የሚቃወሙ አንዳንድ ዘመናዊ የስነ ሰብእ አጥኚዎች ወንጌል ወዳልደረሰባቸው የሕዝብ ክፍሎች ወንጌል እንዳይደርስ አጥብቀው ከሚታገሉበት ምክንያቶች አንዱ፥ “ነባሩ ልማዳቸውና ባህላቸው ስለሚጠፋ ነው' ይላሉ፡፡ እነዚህ 'ሊቃውንት' የማያስተውሉት ነገር አንዳንዶቹ ጎሳዎች በወንጌል ምክንያት ባይተርፉ ኖሮ እንኳን ልማዶችና ባህሎች ሊተርፉላቸው፥ ራሳቸው ሰዎቹም ሊገኙ እስከማይችሉ ድረስ የሚገዳደሉ፥ ግድያ፥ ብቀላ፥ ደም መላሽነት፥ የሰው ሥጋ የመብላት ጭራቅነት፥ ሕጻናትን መግደል ወይም ለአራዊት መስጠት፥ የባህሎቻቸው ገጽታዎች የሆኑ ሰዎችም ነበሩ። ዛሬም እንዲህ ያሉ ባህሎችና ልማዶችን የሚያስተናግዱ ጎሳዎች ይገኛሉ፡፡ በአገራችንም አሉ፡፡
አንድ ባህል እንደ ባህል በመላው ክፉ ወይም በሁለንተናው ጥሩ አይደለም። የአንድ ማኅበረ ሰብ ባህልም ከሌላው የተለየ ነው እንጂ የበለጠ ወይም ያነሰ አይደለም፡፡ ባህልን ስናስብ፥ ባህል የሰው ሥሪት መሆኑን ማወቅ አለብን። ማናቸውም የሰው ሥሪት የሆነ ነገር ፍጹም አይደለምና በፍተሻ ነው መቀበል ያለብን። ሰው ክቡር ነው፤ ግን የወደቀም ነው። እንደ እግዚአብሔር ፍጡር ክቡር፥ በአዳም ደግሞ የወደቀ ነው። ባህሎች እነዚህን ሁለት ገጽታዎች ማንጸባረቃቸው የማይቀር ነው። ስለዚህ በባህሎች ውስጥ ጎጂም ጠቃሚም ገጽታዎች ይታያሉ፡፡
ልብ እንበል፤ ይህች ዓለም በአዳም ስትወድቅ ሁለመናዋ ነው የወደቀው። ይህ ውድቀት የሰውን መንፈሳዊ ማንነት ወይም ሁኔታ ብቻ የሚናገር አይደለም። የሰው ስሜታዊ፥ ሞራላዊ፥ አእምሮአዊ፥ አካላዊ፥ ማኅበራዊ፥ ሌላውም ሁሉ ማንነቱ ነው የተበከለው። ባህላችን እና የትኛውም ባህል፥ ከወደቀ ሰው የመነጨ ነው። ለክርስቲያን፥ ባህል ራሱ ምርቱ ከግርዱ፥ ጎጂው ከጠቃሚው ተለይቶ ለሰው ጥቅም፥ ለእግዚአብሔርም ክብር መዋል የተገባው እንጂ እንደ ተቋም ከክርስቶስ አካል ጋር መደራደርና ቦታ መሻማት ያለበት ነገር አይደለም። ባህል የረከሰ፥ የወደቀ፥ ከክብር የጎደለ ሰው የሠራው ማኅበራዊ ግኝት ነው እንጂ አስቀድሞ የተፈጠረ 'ንጹሕ ባህል' የሚባል ነገር የለም። ንጹህ የሚባል ባህል ኖሮ ሰው ኋላ ተፈጥሮ እዚያ ውስጥ አልገባም። ባህልን የሠራ ሰው ነው፤ ባህል የሰው ሥራ ውጤት ወይም ሥሪት ነው፡፡
እንደ ክርስቲያን የባህል ንጥረ ነገሮች ትርጉማችን እና ግንዛቤያችን ከባህላችን ወይም ከሌላው አገር ባህልም መሆን የለበትም። ቃሉ ስለ ባህል ወይም ወጎች የሚለውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መቀበልም ግዴታችን ነው፤ ማር. 7፥8-13 ይህንን ይነግረናል፡፡ በዚህ ምንባብ፥ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል የተባለውን ትንቢት የጠቀሰበት ነው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። ያለበት ነው። ወጉ ከቃሉ የበለጠበት አካሄድ ይታያል፡፡
ማናቸውም ባህል፥ የኛም ባህሎች ክቡር የሆኑ ያሉባቸውን ያህል ጉድፎችም አሉባቸው። አገራችን ብሔረሰቦችንና ባህሎቻቸውን ማድነቋ ድንቅ ቢሆንም፥ ለክርስቲያኖች ባህሎችን በቅዱስ ቃሉ መፈተሽና መመዘን እንጂ በጅምላ መግዛት አልተፈቀደም። ለባህል ማጎብደድና ለባህል ሲባል ቃሉን በውኃ ማቅጠን ክርስቲያናዊ አካሄድ አይደለም। ለሥልጣንና ለሥራ፥ ለመመረጥና ለመሸለም ተብሎም ጤናማ ያልሆኑ ባህላዊ ንጥረ ነገሮችን መቀበልና፥ በተለይም ከአምልኮ ጋር የተያያዙትን መተግበር የግዴታ ቀንበር ሆነው በአማኞች ላይ ሊጫኑ የተገባ አይደለም፡፡ ባህላዊ አመቻማችነት ጤናማ አይደለም። ባህላዊ አመቻማችነት ለባህል ለማጎብደድ ሲባል እምነትን ለውርርድ የማቅረብ ስሕተት ነው። ባህላዊ አመቻማችነት ክርስትናን ሊጎዳ የሚችል አካሄድን መሄድ ነው። የክርስትና ዋና ግብ ባህልን መለወጥ ሳይሆን ውስጥን መለወጥ ነው። የተለወጠ የውስጥ ሰው፥ የተለወጠ አእምሮና አመለካከት፥ የተለወጠ አካልና የራስ አያያዝ፥ የተለወጠ ቤትናና ቤተ ሰብ፥ የተለወጠ ማኅበረ ሰብም ይፈጥራል፡፡ ግን የሚጀምረው ከውስጥ ነው። መንፈሳዊ ለውጥ መሠረቱ ነው።
ወደ ዘመናችን ባህሎች ስንመጣ፥ ድኅረ ዘመናዊነት ሁሉን ተቀባይ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ይህንን ታክከው ባህሎችና ባህላዊ መገለጫዎች ራሳቸውን የቻሉ ሃይማኖታዊ ተቋማት እስከመሆን እየደረሱ ነው። ቀደም ሲል ከቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጡ ሕዝቦች የቀደሙ ትውልዶችን ልማዶችና ባህሎችን ከመነመኑበትና አንዳንዶቹንም ከሞቱበትም እያወጡ ሲኖሩባቸው ይታያሉ ብያለሁ፡፡ አንዳንዶቹን ባህሎች ወደ ሃይማኖት ቀይረው ሲያመልኩባቸውም ይታያሉ። ክርስቲያኖችም ይጠመዱባቸዋል፤ ሃይማኖቶች የባህል ለምድ ለብሶ በባህል ስም ስለሚቀርቡ አሰናካይነታቸው አይታይም። ስለዚህ መሰናክል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ ቀንዳምና ጥፍራም ሳይሆን ቀንዱን ተከርክሞ፥ ጥፍሩን ተቆርጦ ነው፡፡ ቆይቶ ግን ቀንዱም፥ ጥፍሩም ያድጋሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባህል የሚባል አንድ ባህል ኖሮ ቢሆን ያንን መከተል በተገባን ነበር። ግን የለም። ባህል የማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ ዘዬ ነውና፥ ከባህል ውስጥ ሁሉም ነገሮች ለባህሉ ሰፊ ተካፋዮች ወይም ቢያንስ፥ ለሰፊው ሕዝብ፥ መልካም የመሰሉ እንጂ በባህሉ ውስጥ ላሉትም መቶ በመቶ ተቀባይነት ያላቸው ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ይልቁንም በአንድ የሕዝብ ክፍል ተቀባይነት የኖራቸው ባህሎች በሌላ የሕዝብ ክፍል የተጸየፉ ሊሆኑም ይችላሉ። በዚህ ረገድ የባህላዊ ስነ ሰብእ (Cultural Anthropology) ጥናቶች ብዙ ምሳሌዎችን ያቀርባሉ፡፡
ሌላው፥ በዚያው በአንዱ ባህል ውስጥ ያሉት ነባር ባህሎች ራሳቸው በማኅበረ ሰቡ ማኅበራዊ ስነ ልቡና ማደግ ወይም የሕሊና ንቃት መዳበር የተነሣ አሮጌና ኋላ ቀር ተደርገው ሊናቁና ሊጣሉ ይችላሉ፡፡ በአገራችን በደርግ ዘመን መጀመሪያ የዕድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ የተባለው የተማሪዎችና ምሑራን ዘመቻም በዚህ ረገድ ብዙ አድርጓል። ሰፊ መሠረት ተጥሎለት የተጀመረው የቻይና ቅጂ 'የባህል አብዮት' ይህን ሊያደርግ ሞክሮ ነበር። ጎጂ ባህሎች ብሎ ጥቂት ያልሆኑ ማንቂያዎችን አድርጓል። በባህል ስም ሃይማኖትን ሲነቅፍ ግን ከግድግዳ ጋር ነበር የተላተመው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህላዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ መሆኑን አላስተዋለም። በተለይ ወንጌላዊ ክርስትናን ለመምታት በደርግ የተደረገው ጥረት ከዚህ አንጻር የሚታይ ነው።
ከንቃተ ሕሊና በተጨማሪ መንፈሳዊ መረዳት ወደ ግለ ሰቡ ወይም ማኅበረ ሰቡ ክፍል ሲገባ ከመንፈሳዊ እሴቶቹ ጋር ነው የሚገባው። መንፈሳዊ ስል ጠቅላላ መንፈሳዊ ኹነትን መናገሬ ቢሆንም ይህኛው ጉዳያችን ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ስለሆነ በተለይ ስለ ክርስትና መናገሬ ነው። ወንጌል ወደ አንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ወይም ወደ አንድ የሕዝብ ክፍል ሲገባ መንፈሳዊው እሴት ባህላዊውን ቀለም ብዙውን ጊዜ ይበርዘዋል፤ ቆይቶም ይለውጠዋል። የወሊዱና የጋብቻው፥ የቀብሩና የልቅሶው፥ የሥራና ግንኙነቶች መስተጋብሮች ቅርጽና ይዘት በቃሉ መታየትና መከርከም ይጀምራሉ፡፡ ክርስቲያኖቹ እንደ ክርስቲያን ሲኖሩና ሲሠሩ ለውጥ ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡
ይህ ለውጥ፥ ወይም በአንዳንዶች እይታ፥ ብረዛና ቅየራ፥ ጥሩ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ እንደ ባህሉ ጠቃሚነትና እንደ ተሟጋቾቹ ጥንካሬ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች የባህል አብዮታውያን ሽንጣቸውን አሸንፍጠው ጎጂ እንኳ ቢሆኑ ባህሎች በሃይማኖቶች መለወጥ ቀርቶ መደፈርና መነካትም የለባቸውም የሚል ግልጽ አቋም ይይዛሉ፡፡ በዚህም ክርስትና የገባባቸውን አንዳንድ ሕዝቦችን ባህሎች መለወጥ በጸጸት በማሰብ ከርስትናን ይኮንናሉ። በአንጻሩ ደግሞ በማገዳደል በዘር ማጽዳት ፈጽመው ሊጠፉ ይችሉ የነበሩ ሕዝቦች ባህሎች በወንጌል አማካይነት በመወገዳቸው ምክንያት ባህሉ ቢጠፋም ሕዝቡ ሊተርፉና ሊደላደሉ ስለቻሉ ሕዝቦች በማሰብ የሚያደንቁና የሚያመሰግኑ አሉ። አንዳንድ ሃይማኖቶች ከባህሎች ጋር ባህላዊ ቅርሶችንም ከማውደም አይመለሱም። የታሊባን መንግሥት ለምሳሌ፥ ከእስልምና በፊት የነበሩ የቡድሂዝም የባህልና ሃይማኖት ቅርሶችን ዩኔስኮ እየተማጸነም እንኳ፥ አውድሞአቸዋል። አንዳንድ ሃይማኖቶች ደግሞ በአንጻሩ፥ ባህሎችን አጥበውና አጽድተው የሃይማኖቱ መገልገያ ያደርጉታል፡፡
ወደ አይሁድ ባህል ስንመጣ፥ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የነበራቸው ቢሆኑም ከውድቀት በኋላ ይህ ግንኙነት ተበላሽቶአል፤ ተሰብሮአል። ከሰዎች መብዛት እንዲሁም፥ ብታኔና ዝርወት በኋላ ባህልና ሃይማኖት የተቆራኙ ገመዶች ሆነው ሕዝብን ሲያስተሳስሩ ኖረዋል። እግዚአብሔር ጥቂት ሆነው ወደ ግብጽ የወረዱትን አይሁድ እንደ ሕዝብ ሲያወጣቸውና ሕግ ሲሰጣቸው ቀድሞ ባህል የሌላቸው ሰዎች አልነበሩም። ሲወልዱ ወይም ሲያሳድጉ፥ ሲሞቱና ሲቀብሩ፥ ሲዳሩና ሲጋቡ፥ ሲገበያዩና ሲዋጉ የሚያደርጉት ወግ የሌላቸው አልነበሩም፡፡
የተሰጧቸው ሕግጋትም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ብቻ የሚመለከቱም አልነበሩም፡፡ ሕጉ ማኅበራዊ አወቃቀራቸውንም የዳሰሰ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ለርስቱ የተለየ ሕዝብ አድርጎ ሲመርጣቸው በአኗኗራቸው በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ የተለየ እንዲሆኑ ነው። ይህ መለየት ባህልንም ይነካል። በዋናነት የተጠሩት የእርሱ ወኪል ሕዝብ ሆነው እንዲኖሩ ስለሆነ የእርሱ ሲሆኑ የእርሱ መሆናቸውን የሚያንጸባርቁት የተለየ ማንነት አላቸው፡፡ ስለዚህም፥ ሌሎቹ ባህሎቻቸው የሕጉ ተገዢ ሆነው የማንነቱና በእርሱ ያገኙት ማንነታቸው ነጸብራቅ ይሆናሉ፡፡ ይህ ትክክለኛ የባህል በመለኮታዊ ሕግ ስር የመሆን መንገድ ነው። ልብ ማለት ያለብን፥ እነዚህ ሰዎች የተጠሩትና እየተቀረጹ የነበረው በጠቅላላ፥ ማለትም፥ እንደ ሕዝብ ሆነው ነው፡፡
ብዙ ሳይቆዩ ግን እነዚህ ሰዎች ወይም አይሁድ፥ ለእግዚአብሔር የርስቱ ሕዝብ መሆናቸው ቀርቶ፥ ሕጉን እንደ ማነቆ አዩት፤ ወደ ነበሩበት ወደ ግብጽ መመለስም ተመኙ። እንደተመኙት አልተመለሱም፤ ወደ ተስፋዋ ምድር ገቡ። ልባቸው ግን ከአምላካቸው ጋር አልነበረም። ከገቡ በኋላም፥ ለእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን በመኖር እግዚአብሔርን ማንጸባረቅ ሲገባቸው፥ በዚህ ፈንታ፥ በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ ጋር ነበር የተመሳሰሉት። ተደባለቁ፥ ተቀየጡ እንጂ ማንነታቸውን አልጠበቁም። ተወረሱ እንጂ አልወረሱም፡፡ ምድሪቱንም እንኳ በወጉ አልወረሱም።
እነዚህ ሰዎች በእውነት እንደታሰበላቸው ኖረው ቢሆን ከአይሁዳዊ ሕዝባዊ ባህል በተለየ መልኩ 'መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባህል' የሚባል ነገር ሊኖር በቻለና የዚያንም ባህል መልክ በተገነዘብን ነበር። ግን አልሆነም፡፡ ይህን በተመለከተ፥ ከላይም እንዳመለከትኩት፥ ላሰምርበት የምወደው ዋና ጉዳይ ሃይማኖትን (በዚህ ዐውድ ክርስትናን) የሚወርረው ባህል ሳይሆን ባህልን የሚወርረው ሃይማኖት መሆኑን ነው። ሃይማኖቱ ባህሉን በመላው ላይቀይረው ይችላል፡፡ ክርስትናና ባህል ለምርጫ ቢቀርቡ መራጩ ክርስቲያን መምረጥ የተገባው እምነቱን መሆኑ ግን ግልጽ ነው። እምነቱ በባህሉ ላይ ጫና ሊፈጥር ይገባዋል እንጂ ባህሉ እምነቱን ሊቀርጽለት መልቀቅ እና መፍቀድ የለበትም። ባህል መልካም ገጽታዎች እንዳሉት ግልጽ ነው፤ ክርስትና ግን በመላው መልካም ስለሆነ በባህሉ ውስጥ የሚገኙት መልካም ነገሮች በዚህ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ስደመድም፥ እንግዲህ የአይሁድ ባህል የምንለው ምኑን ነው? የአይሁድ ባህል የምንለው አብርሃም ከአገሩና ከሕዝቡ ተለይቶ ሲወጣ ካደገበትና ከኖረበት ጀምሮ ወደ በተስፋይቱ ምድር የኖረበትን፥ እርሱም ይስሐቅም በተስፋዋ ምድር ቀዬ እና እስከ ግብጽ በኖሩባቸው የነበረውን፥ ያዕቆብም በሁለት ወንዞች መካከል በኖረበት ዘመንና ወግ የደለበውን፥ ወደ ግብጽ ወርደው በኖሩበት ከ400 በላይ ዓመታት የተጠቀጠቀውን፥ ወደ ተስፋዋ ምድር ከገቡ በኋላ ከዙሪያቸው አሕዛብ ጋር ተደባልቀው በኖሩባቸው ዘመናት ያካበቷቸውን፥ በምርኮ ምድር የቋጠሯቸውን ባህሎች ሁሉ ማለታችን ነው።
ወደ ክርስትና ስንመጣ ወንጌል ወደ አይሁድም ወደ አሕዛብም ሲገባ በመጀመሪያ የለወጠው ባህልን አይደለም ብለናል። ባህልን የመለወጥ የወንጌል ተልእኮም አይደለም፡፡ የወንጌል ተልእኮ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። ጌታ የሰጠው። ዓለማችን የሚያስፈልጋት የባህል ቅየራ ሳይሆን የዓለማችን ወይም የሰው ልጆች መሠረታዊ ችግር የሆነው የኃጢአት መወገድ ነው። የኃጢአት መፍትሔውም አዳኙ ኢየሱስ ነው።
ወንጌል ውስጥን፥ መንፈስን፥ መንፈሳዊ ማንነትን ነው በመጀመሪያ የሚለውጠው፡፡ ይህ ውስጣዊ ለውጥ ከውስጥ ይጀምርና አድማሱ እየሰፋ ይሄዳል። ይህ የተለወጠ ማንነት ባህሉን ሊፈትሽና ከቃሉ ጋር ከተጣጣመ ሊቀበለውና አዲሱንና ዋናውን ተልእኮውን ሊያሰርጽበት፤ ካልተጣጣመ ደግмо ሊገፋውና ወዲያ ሊለው ይገባል፡፡ ባህል በአዲሱ ማንነቱ ላይ በግዴታ ሊጫንበት አይገባም። ይህ በነጠላም በወልም ነው። ክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ በአሮጌው ማንነቱ የተገዛላቸው የባህሉ መንጸባረቂያዎች በአዲሱ ማንነቱ ላይ ገዥ ሆነው ሊቀጥሉ መፈቀድ የለበትም፡፡
ባህላዊ አመቻማችነት ከክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይህች ዓለም በአዳም ስትወድቅ ሁለመናዋ መውደቁ፥ የሰውን መንፈሳዊ ማንነት ወይም ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፥ የሰውን ስሜታዊ፥ ሞራላዊ፥ አእምሮአዊ፥ አካላዊ፥ ማኅበራዊ፥ ባህላዊ ማንነቱ ሁሉ ነው የዳሰሰ ብክለት ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የማንነቱ መገለጫዎች ናቸውና ሰው በክርስቶስ ሲዋጅ ከእነዚህ ተጽዕኖዎች ሁሉ አብሮ ነጻ መውጣት አለበት፡፡ በወደቀ ሰው ዘንድ ንጹህ ባህል የሚባል ነገር የለም፤ ባህል የሰው ሥራ ነው። ባህል የረከሰ ሰው ማኅበራዊ ግኝትና ሥሪት ነው። ሰው በኃጢአት የወደቀ ነውና በክርስቶስ ያልተዋጀ ሰው ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሰት እና የመርገም ጨርቅ ነው፡፡ ባህላችን (የትኛውም ባህል) ከወደቀ ሰው የመነጨ በመሆኑ፥ ባህል ራሱ ተዋጅቶ ለእግዚአብሔር ክብር መዋል የተገባው እንጂ እንደ ተቋም ከክርስቶስ አካል ጋር መደራደርና ቦታ መሻማት ያለበት ነገር አይደለም። ባህላዊ አመቻማችነት ከክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም።
ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።