የህይወት ቃል ህብረት Logo

መንፈሳዊ ጥናት

የአምልኮና የምስጋና ሕይወት

እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ማምለክ

†

"የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባንን ይዛችሁ ወደ አደባባዩ ግቡ። በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤"

መዝሙረ ዳዊት 96፥8-9

አምልኮና ምስጋና የክርስትና እምነት ተጨማሪ ጌጦች ሳይሆኑ፣ በክርስቶስ ደም ለተዋጀው ሰው ልጅ የተሰጠው የሕልውናው መሠረት ናቸው። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ለራሱ ክብር ነው (ኢሳ. 43፥7)፤ ስለዚህ አምልኮ ከሰው ልጅ ተጨማሪ ተግባራት አንዱ ሳይሆን፣ የመኖሩ ዋና ምክንያትና ግብ ራሱ ነው። በዘመናችን አምልኮ ሲባል የብዙዎች አእምሮ የሚሄደው ወደ ስሜታዊ የሙዚቃ መግለጫዎች ወይም በየሳምንቱ እሁድ ወደሚደረጉ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ብቻ ነው። ነገር ግን እውነተኛ አምልኮ ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። አምልኮ ማለት በክርስቶስ ዋጋ የተገዛው አማኝ፤ ለመድኃኒቱ ግርማ፣ ለጸጋው ጥልቀት፣ ለማይለወጠው ሉዓላዊነቱ የሚሰጠው የዕለት ተዕለት የሕይወት ምላሽ ነው። ልብ ያልተነካበት ዝማሬ ድምፅ ብቻ እንደሆነ ሁሉ፣ ልብ የተነካበት ዝምታም እንኳ አምልኮ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚመዝነው ድምፃችንን ሳይሆን ልባችንን ነውና (1 ሳሙ. 16፥7)።

"የአምልኮና የምስጋና ሕይወት" የሚለው ሐረግ ይህንን ጥልቅ እውነት በውስጡ አቅፎ ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ "እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።" (ሮሜ 12፡1) በማለት እንዳዘዘው፣ አምልኮ በመዝሙር ብቻ የሚገደብ ሳይሆን መላው ሕይወታችንን በመሠዊያ ላይ የማኖር ጉዳይ ነው። በብሉይ ኪዳን መሥዋዕት ታርዶና ሞቶ የሚቀርብ ሲሆን፣ በአዲስ ኪዳን ግን አማኙ በሕይወት እየኖረ፣ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በማስገዛት "ሕያው መሥዋዕት" ሆኖ ራሱን ያቀርባል። ልብ በሉ፦ ሕያው መሥዋዕት ከምድረ መሠዊያ ላይ የመውረድ ልማድ አለው፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወዲያውኑ "በዚህ ዓለም ምሳሌ አትሁኑ" ብሎ ይቀጥላል (ሮሜ 12፥2)። በብሉይ ኪዳን፦ መሥዋዕት የሚሆነው እንስሳ በመጀመሪያ ይታረዳል፤ ደሙ ይፈስሳል። አንዴ ከሞተ በኋላ በመሠዊያው ላይ ሲቀመጥ፣ የሞተ ነገር የራሱ ፈቃድ (Will) ስለሌለው ከዚያ መሠዊያ ላይ ተነስቶ የመሄድ አቅም የለውም።

በአዲስ ኪዳን (ሮሜ 12፡1)፦ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው እንድንሞት ሳይሆን በሕይወት እየኖርን "ሕያው መሥዋዕት" ሆነን እንድንቀርብ ነው። እዚህ ላይ ነው ትልቁ ፈተና ያለው። "ሕያው" የሆነ ነገር የራሱ የሆነ ነፃ ፈቃድ አለው፤ የራሱ ምርጫ፣ ስሜትና ፍላጎት አለው። ዛሬ በጸሎት፣ በዝማሬ፣ ወይም በቤተክርስቲያን ፕሮግራም ላይ "ጌታ ሆይ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ሰጥቼሃለሁ፤ ፈቃድህ ይሁን" ብለን ራሳችንን በመሠዊያው ላይ እናኖራለን። ነገር ግን ከጥቂት ሰዓታት ወይም ቀናት በኋላ፣ የሚያጓጓ ነገር ስናይ፣ ፈተና ሲገጥመን፣ ወይም የራሳችንን መንገድ መከተል ስንፈልግ፣ ሳናስበው ራሳችንን ከመሠዊያው ላይ እናወርዳለን (ማለትም የሰጠነውን ሕይወት መልሰን እንወስዳለን)። ሕያው መሥዋዕት ከመሠዊያ ላይ የመውረድ አመል ስላለው፣ ራስን ለእግዚአብሔር ማቅረብ የአንድ ጊዜ ክንውን ሳይሆን በየቀኑ፣ በየሰዓቱ የሚታደስ ውሳኔ መሆን አለበት። ጌታ ኢየሱስም "ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ" (ሉቃስ 9፡23) ያለው ለዚህ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አማኞች ከመሠዊያው ላይ ለምን እንደሚወርዱ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ ወዲያውኑ "በዚህ ዓለም ምሳሌ አትሁኑ" ብሎ ያስጠነቅቃል። መሥዋዕቱ ከመሠዊያው ላይ ወርዶ እንዲሄድ የሚስበው ትልቁ ማግኔት "የዚህ ዓለም ሥርዓትና አስተሳሰብ" ነው። ዓለም የራሱ የሆነ የኑሮ ዘይቤ፣ የገንዘብ ፍቅር፣ የሥጋ ምኞት፣ እና ራስ ወዳድነት አለው። ከዓለም ጋር መመሳሰል ስንጀምር ከመሠዊያው ላይ እንወርዳለን። ስለዚህ ጳውሎስ በመሠዊያው ላይ ጸንታችሁ ለመቆየት ከፈለጋችሁ "በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ የዚህን ዓለም አሠራር አትምሰሉ" ይላል። አእምሯችን በእግዚአብሔር ቃል ካልታደሰ በቀር፣ ሥጋችን ሕያው ስለሆነ ከመሠዊያው ላይ መውረዱ አይቀርም።አምልኮ ስለዚህ በየቀኑ የሚታደስ ራስን የመስጠት ውሳኔ ነው እንጂ አንዴ ተፈጽሞ የሚያልቅ ክንውን አይደለም። ስለዚህ አምልኮ እኛ የምናደርገው የሃይማኖት ክንውን ሳይሆን፣ እኛ ራሳችን የምንሆነው ማንነት ነው።

የቅዱሳት መጻሕፍት ታሪክ፣ ከፍጥረት ጸጥታ አንስቶ እስከ ዘላለማዊው የዙፋን አምልኮ ድረስ፣ የእግዚአብሔር ዋና ጥሪ አምልኮ መሆኑን በግልጽ ያውጃል። ከአቤል ንጹሕ መሥዋዕት፣ ከአብርሃም የመታዘዝ መሠዊያ ጀምሮ፣ በሙሴ ማደሪያ ድንኳን ሥርዓት አልፎ፣ በዳዊት ጥልቅ የንስሐና የደስታ መዝሙራት ውስጥ እያደገ ይመጣል፤ በመጨረሻም በራእይ 5 ላይ በሰማያዊው ጉባኤ ታላቅ ፍጻሜውን ያገኛል። እኛም ዛሬ በምድር የምናቀርበው አምልኮ የዚያ የዘላለማዊው ሰማያዊ አምልኮ ልምምድ ነው፤ ገና ያልደረስንበት ሀገር ቋንቋ አስቀድመን የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው ማለት ይቻላል።

"እውነተኛ ሰጋጆች ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል... አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና።"

ዮሐንስ 4፥23

እውነተኛ አምልኮ ከቦታና ከሥርዓት በላይ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚገዛውና በእግዚአብሔር ቃል እውነት ላይ የተመሠረተ የልብ ዝንባሌ ነው። እጆችን ማንሳት ሳይሆን የተቀደሰ ሕይወትን ማንሳት ነው፤ በዜማ መዘመር ብቻ ሳይሆን የሕይወትን ቅላጼ በሙሉ ለመታዘዝ ማስገዛት ነው። "መንፈስ" ያለ "እውነት" ስሜታዊነት ብቻ ይሆናል፤ "እውነት" ያለ "መንፈስ" ደግሞ ደረቅ ትምህርት ብቻ ይቀራል። ኢየሱስ የፈለገው ሁለቱን በአንድነት የያዘ አምልኮ ነው — በቃሉ እውነት ላይ የቆመና በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት የሚነድ።

የአምልኮ ባህሪ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ እውነት ግልጽ ነው፡- እግዚአብሔር የሚፈልገው ልብን እንጂ ልማድን አይደለም። እስራኤልን ብዙ ጊዜ ልብ በሌለባቸው ሥርዓቶች ምክንያት ይገስጻት ነበር (ኢሳ. 29:13፣ አሞ. 5:21-24)። ኢየሱስም ቅንነት የጎደለው ግብዝነት የተሞላበት አምልኮን አውግዟል (ማቴ. 15:8-9)። ነቢዩ ሳሙኤል ለንጉሥ ሳኦል "መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም ከአውራ በጎች ስብ ይበልጣል" (1 ሳሙ. 15፥22) ብሎ የተናገረው ቃል፣ የውጭ ሥርዓት ያለ ውስጣዊ መታዘዝ ዋጋ እንደሌለው ለዘላለም የሚያውጅ መርህ ነው። ስለዚህ የአምልኮ ጥያቄ ዘወትር "ምን እያደረግን ነው?" ሳይሆን "በምናደርገው ጊዜ ልባችን የት አለ?" የሚል ነው።

ወደ አብ በወልድ በኩል በመንፈስ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ አምልኮ ወደ ማንኛውም አምላክ የሚቀርብ ረቂቅ መንፈሳዊነት ብቻ አይደለም፤ በሥላሴ ቅርጽ የተዋቀረ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በግልጽ ያስቀምጠዋል፦

"በእርሱ በኩል ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።"

ኤፌሶን 2፥18

"በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።"

ፊልጵስዩስ 3፥3

እውነተኛ አምልኮ ወደ አብ ይቀርባል (ግቡ)፣ በወልድ በኩል ይቀርባል (መንገዱ/አስታራቂው)፣ በመንፈስ ቅዱስ ይገለጣል (ኃይሉ)። አንዱን ካጎደለ አምልኮ ራሱ ይጎድላል፤ ያለ ክርስቶስ ወደ አብ መቅረብ የለም (ዮሐ 14፥6)፣ ያለ መንፈስ ቅዱስም "በእውነት" ማምለክ አይቻልም (ዮሐ 4፥24)። ይህ ማለት አምልኮ የክርስትና ልምምድ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ የሥላሴ ሕይወት ውስጣዊ ግንኙነት ነጸብራቅ ነው፤ በፍቅር ኅብረት ውስጥ ወደ ነበረው መለኮታዊ ኅብረት አማኙ በክርስቶስ ተጠርቶ የሚገባበት በር ነው።

የመስዋዕትነት ዋጋ ያለው አምልኮ

ንጉሥ ዳዊት ከአራውና ዘንድ የአውድማ ስፍራ በነጻ ሊሰጠው ሲፈልግ የሰጠው መልስ የእውነተኛ አምልኮ ልብ ምን እንደሆነ ያሳያል፦

"ይህስ አይሆንም፤ ነገር ግን በዋጋ እገዛዋለሁ፤ ለእግዚአብሔርም ለአምላኬ በከንቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አላቀርብም።"

2ኛ ሳሙኤል 24፥24

አምልኮ ምንም የማያስከፍለን ከሆነ፣ አምልኮ ላይሆን ይችላል። ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን፣ ምቾታችንን፣ ራሳችንን የመግዛት ፍላጎታችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ስንሰጥ ብቻ ነው እውነተኛ አምልኮ የሚሆነው። ይህ መርህ ዛሬም ለምንኖርበት ምቾት-ተኮር ዘመን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ማርያም የናርዶስን ሽቱ በኢየሱስ እግር ላይ ስታፈስስ (ዮሐ. 12፥3)፣ ቤቱ ሁሉ በሽቱ መዓዛ እንደተሞላ ሁሉ፣ ውድ የሆነ አምልኮ ሁልጊዜ ዙሪያውን ይሞላል፤ ርካሽ አምልኮ ግን ምንም አሻራ አይተውም።

የአምልኮ ታሪካዊ ጉዞ (ከኤደን እስከ ዘላለም)

አምልኮ የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እያደገ የመጣ ጥልቅ የታሪክ ሂደት አለው፦

  • የመጀመሪያው አምልኮ (አቤልና ቃየን) በሰው ልጅ ታሪክ የመጀመሪያው የተመዘገበው አምልኮ በዘፍጥረት 4 ላይ ይገኛል። አቤልና ቃየን መሥዋዕት ይዘው ቀረቡ። የቃየን መሥዋዕት ውድቅ ሲደረግ፣ የአቤል ግን ተቀባይነት አገኘ። ዕብራውያን 11:4 እንደሚለው "አቤል ከቃየን ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት በእምነት አቀረበ።" እግዚአብሔር ያየው የፍሬውን ዓይነት ሳይሆን የአምላኪውን ልብ፣ እምነትንና አክብሮትን ነበር። ገና ከመጀመሪያው፣ የደም መሥዋዕት አስፈላጊነትና ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይቻል ተደንግጓል (ዕብ 9፥22)።
  • የአምልኮ ትርጉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "አምልኮ" (በዕብራይስጥ ሻካህ / Shachah - መስገድ) የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 22:5 ላይ ነው። አብርሃም አንድያ ልጁን ይስሐቅን ሊሠዋ ወደ ሞሪያ ተራራ ሲወጣ፣ "እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን፥ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን" አላቸው። አምልኮ ከዝማሬ ጋር ሳይሆን፣ እጅግ ከሚወዱት ነገር በላይ እግዚአብሔርን ማስቀደም መሆኑን ያሳያል። አብርሃም ተስፋውን ሁሉ በያዘው ልጁ ላይ እጁን ሲዘረጋ፣ "እግዚአብሔር ራሱ መሥዋዕቱን ያዘጋጃል" (ዘፍ 22፥8) የሚል እምነት ነበረው፤ ይህም በኋላ በጎልጎታ ራሱ በእግዚአብሔር ልጅ የተፈጸመውን ታላቅ ምትክ አስቀድሞ ይጠቁማል።
  • ከድንኳን ወደ ልብ በብሉይ ኪዳን አምልኮ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ በካህናት አማካይነት፣ በእንስሳት ደምና በዕጣን ጢስ የሚቀርብ ሥርዓታዊ አምልኮ ነበር። እያንዳንዱ የድንኳኑ ክፍል የአምልኮን ደረጃ ያሳይ ነበር፦ በውጭ አደባባይ የናስ መሠዊያ ኃጢአትን ያስተሰርያል፣ የናስ መታጠቢያ ያነጻል፤ በቅድስት ስፍራ መቅረዙ ብርሃን ይሰጣል፣ የኅብስቱ ገበታ ኅብረትን ያመለክታል፣ የዕጣኑ መሠዊያ ጸሎትን ይወክላል፤ ከመጋረጃው ባሻገር ደግሞ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የቃል ኪዳኑ ታቦት የእግዚአብሔርን ልዩ ክብር ይይዝ ነበር። ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመድረስ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በደም አልፎ መግባት ይችል ነበር (ዕብ 9፥7)። አዲስ ኪዳን ሲመጣ ግን ኢየሱስ ሲሞት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ (ማቴ 27፥51)፤ ይህም ወደ እግዚአብሔር ቀጥተኛ መንገድ ለዘላለም እንደተከፈተ ያውጃል። ጳውሎስ "ሰውነታችሁን ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ" (ሮሜ 12:1) በማለት፣ የሕንፃውን አምልኮ ወደ ዕለት ተዕለት የቅድስና ሕይወት አሸጋገረው። አማኙ ራሱ ዛሬ "የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ" ተብሏል (1 ቆሮ. 6:19)።

ንድፍ ፩፡ የአምልኮ ታሪካዊ ጉዞ — ከኤደን እስከ ዘላለም

ኤደን ፍጥረት/ኅብረት አቤል የእምነት መሥዋዕት አብርሃም "አምልኮ" ተጠቀሰ ሙሴ ማደሪያ ድንኳን ዳዊት ክፍት ድንኳን፣ 24/7 ኢየሱስ መጋረጃው ተቀደደ ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቤተ መቅደስ ዘላለም ራእይ 4-5

ንድፍ ፪፡ አምስቱ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች — የአምልኮ ትምህርት ቤት

ዘሌዋውያን 1-7 ላይ የተዘረዘሩት አምስቱ መሥዋዕቶች፣ ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጡ የአምልኮ "ፊደላት" ነበሩ፤ እያንዳንዱም ስለ ክርስቶስ ሥራና ስለ አማኙ ምላሽ የተለየ እውነት ያስተምራል፦

ኦላህ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘሌ. 1 ሙሉ በሙሉ ለእሳት ይሰጣል ትርጉም ፍጹም ራስን መስጠት/ መገዛት ምንሐህ የእህል መሥዋዕት ዘሌ. 2 የድካም ፍሬ ያለ ደም ይቀርባል ትርጉም የዕለት ተግባርን ለእግዚአብሔር መስጠት ሸላሚም የደኅንነት/የኅብረት መሥዋዕት ዘሌ. 3 አቅራቢውና ካህኑ አብረው ይመገባሉ ትርጉም ከእግዚአብሔር ጋር ደስ ብሎ ኅብረት ሐጣት የኃጢአት መሥዋዕት ዘሌ. 4 ላልታወቀ ኃጢአት ማስተስረያ ትርጉም የተፈጥሮ ኃጢአት ስርየት አሻም የበደል መሥዋዕት ዘሌ. 5-6 ካሳ ተጨምሮ ይከፈላል ትርጉም የተበደለውን ማካካስ

አምስቱም መሥዋዕቶች በክርስቶስ አንድ ጊዜ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል (ዕብ. 10:10-14)፤ ዛሬ አማኙ ራሱን የሚያቀርበው ምላሽ ግን በእያንዳንዱ መሥዋዕት ውስጥ ተንጸባርቋል — ሙሉ ስጦታ፣ የዕለት ተግባር፣ ኅብረት፣ ንስሐና ማካካሻ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ አምልኮ ይህ አይደለም፡

  • ትወና ወይም ማስመሰል አይደለም (Performance)
  • ከቅን ልብ ውጪ ያለ ልማድ አይደለም
  • የሥርዓቶች ዝርዝር ብቻ አይደለም
  • ስሜትን ብቻ ተከትሎ የሚነሳ ወይም የሚጠፋ ግለት አይደለም
  • "ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤" (ማቴ 15:8)

ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አምልኮ፡

  • ከእግዚአብሔር ጋር ያለ የጠበቀ ግንኙነት ነው
  • የዘላለም የመገዛት የአኗኗር ዘይቤ ነው
  • ዋጋ የሚያስከፍል የመታዘዝ ተግባር ነው
  • በመንፈስና በእውነት የሚቀርብ የልብ ፍሬ ነው
  • በደስታም በመከራም ጊዜ የማያቋርጥ የልብ ዝንባሌ ነው

በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን የአምልኮ ንጽጽር

ገጽታ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን
ቦታ ማደሪያ ድንኳን / ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ብቻ የትም ቦታ (አማኙ ራሱ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነው - 1 ቆሮ 3:16)
ቅርጽ የእንስሳት መሥዋዕቶች፣ ሥርዓቶች፣ ዕጣንና ደም ሕይወትን እንደ መሥዋዕት ማቅረብ፣ የምስጋና ፍሬ (ዕብ. 13:15)
አስታራቂ የሌዋውያን ክህነት (አሮንና ልጆቹ ብቻ) ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ብቸኛ ሊቀ ካህን፣ የሁሉም አማኝ ካህንነት (1 ጴጥ 2:9)
ትኩረት ለቃል ኪዳን ውጫዊ ሕግጋት መታዘዝ በክርስቶስ ጸጋ ላይ የተመሠረተ የልብ ግንኙነት
ድግግሞሽ ኃጢአት በተደጋገመ ቁጥር የሚደገም መሥዋዕት "አንዴ ለሁል ጊዜ" የተፈጸመ መሥዋዕት (ዕብ. 10:10)

ትእዛዝ እና የአኗኗር ዘይቤ

አምልኮ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ምስጋና ደግሞ እግዚአብሔር በሰራው ሥራ ላይ ያተኩራል። መጽሐፍ ቅዱስ ምስጋናን እንደ አማራጭ ስሜት ሳይሆን እንደ ትእዛዝ ያቀርበዋል፦ "እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን።" (መዝ 150:6) የሚለው ትእዛዝ ምንም ሁኔታ ቢፈጠር የማይታገድ ዘላቂ ጥሪ ነው። ምስጋና ችግር ከሌለ ብቻ የሚቀርብ "ጉርሻ" ሳይሆን፣ የመተንፈሳችን ያህል ተፈጥሯዊ ተግባር እንዲሆን ታዝዘናል፤ ጳውሎስም "በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ እናንተ ነውና" (1 ተሰ. 5:18) በማለት ምስጋናን ከሁኔታ ነጻ ያደርገዋል።

ማርያም (ሚርያም) እና የመጀመሪያው የጋራ ምስጋና

በዘጸአት 15 ላይ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን በተአምር ከተሻገሩና የፈርዖን ሠራዊት በውኃው ውስጥ ከሰጠመ በኋላ፣ የሙሴ እኅት ማርያም አታሞ በእጇ ወስዳ፣ ሴቶችም ሁሉ አታሞ እየመቱ በዘፈን ተከተሏት። "ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ" እያለች መራቻቸው። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የመጀመሪያው የጋራ የምስጋና መዝሙር ነው። ትኩረት የሚስበው ነገር ምስጋናው የመጣው ከድል በኋላ ሳይሆን ገና ወደ ምድረ በዳ ከመግባታቸው በፊት፣ የመጪውን ውጊያ ሳያውቁ በእምነት መሆኑ ነው።

የዳዊት ድንኳን

በ1ኛ ዜና 16 መሠረት፣ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ጽዮን ሲመልስ፣ ታቦቱን ክፍት በሆነ ድንኳን ውስጥ አኑሮ፣ 4,000 ዘማሪዎችንና 288 የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችን በመመደብ በቀንና በሌሊት ያለምንም ማቋረጥ የምስጋናና የአምልኮ አገልግሎት እንዲካሄድ አደረገ። የሚያስደንቀው ነገር ዳዊት ታቦቱን መጋረጃ በሌለው ድንኳን ውስጥ በማኖሩ፣ ካህኑ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ወደ ተራራው የመጣ ሰው በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ፊት እንዲቀርብ በር ከፈተ፤ ይህም ከዘመናት በኋላ በክርስቶስ ደም ለሁሉም ምእመናን ይፋ ለሚደረገው ነጻ መዳረሻ ጥላ ነበር። ለዚህም ነው እግዚአብሔር "የወደቀችውንም የዳዊትን ድንኳን እንደ ገና እሠራታለሁ" (ሐዋ 15:16) ብሎ ቃል የገባው፤ ይህም የአዲስ ኪዳን አምልኮ ምሳሌ ነው።

ንድፍ ፫፡ ሰባቱ የዕብራይስጥ የምስጋና ቃላት

ምስጋና ውዳሴ / Praise ሃላል ማብራት/ በደስታ ማወደስ ያዳህ እጆችን ዘርግቶ ማመስገን ባራክ ተንበርክኮ መባረክ ቶዳህ ምላሽ ሳይታይ የሚሰጥ ዛማር በመሣሪያ መዘመር ሻባክ ጮክ ብሎ የድል ጩኸት ተሂላህ አዲስ የምስጋና መዝሙር

ምንጭ፡ የዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን መዝገበ ቃላት (Strong's Concordance) — ዋቢ ጥቅሶች፦ መዝ 150:6፣ 138:1፣ 103:1፣ 22:3፣ 92:1፣ 117:1፣ 50:14።

እነዚህ ሰባት ቃላት አንድ ላይ ተጣምረው የሚያሳዩት ምስጋና በአንድ መንገድ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ መላውን ማንነታችንን ፣ ድምፃችንን፣ እጆቻችንን፣ ጉልበታችንን፣ ስሜታችንን የሚያካትት ሁለንተናዊ ምላሽ መሆኑን ነው። "ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ በውስጤም የሚኖረው ሁሉ ቅዱስ ስሙን ይባርክ" (መዝ 103:1) ሲል ዘማሪው ራሱን ብቻ ሳይሆን "በውስጡ ያለውን ሁሉ" ወደ ምስጋና ይጠራል።

በግሪክ (አዲስ ኪዳን) የምስጋና ቃላት

  • አይኔኦ (Aineo) – ማመስገን ወይም ማወደስ (ሉቃስ 2:13)
  • ዩሎጂዮ (Eulogeo) – መባረክ ወይም መልካም መናገር (ኤፌ. 1:3)
  • ዶክሳዞ (Doxazo) – ማክበር ወይም ክብር መስጠት (ዮሐ. 17:1)
  • ኤክሶሞሎጌኦ (Exomologeo) – በአደባባይ መናዘዝና ማወደስ (ሮሜ 14:11)

እነዚህ ቃላቶች ምስጋና ገላጭ፣ ድምጻዊ እና የሚታይ መሆኑን ያሳያሉ። በጭራሽ ዝም የሚል ተግባር አይደለም።

አምልኮ vs. ምስጋና

አምልኮ እና ምስጋና በክርስትና ልምምድ ውስጥ ብዙውን ጊዜ አብረው ጥቅም ላይ ይውላሉ፣ ነገር ግን የተለያየ ዓላማ አላቸው።

  • ምስጋና የሚያተኩረው በእግዚአብሔር ኃያል ሥራው፣ በታማኝነቱ እና በፍቅሩ ላይ ነው። (መዝሙር 100:4)
  • አምልኮ ደግሞ ጥልቅ እና የጠበቀ ነው፤ ሁኔታዎቻችን ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር ማን እንደሆነ በማሰብ የሚመጣ አድናቆት፣ አክብሮት እና መገዛት ነው። (ዮሐንስ 4:24)

በቀላሉ ለማስቀመጥ፦ ምስጋና ብዙውን ጊዜ "እግዚአብሔር ስላደረገው" ነው፤ አምልኮ ግን "እግዚአብሔር ስለሆነው" ነው። ምስጋና ወደ ደጅ ያስገባናል፣ አምልኮ ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይወስደናል (መዝ 100:4)።

†

በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ አምልኮና ምስጋና

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፣ በአብ ላይ በመመካት፣ በጸሎት፣ በአምልኮና በምስጋና የተሞላ ሙሉ የሰው ሕይወት ኖሯል። እሱ እንደ አምላክ አምልኮን ከመቀበል በተጨማሪ (ማቴ. 14:33፤ ዮሐ. 9:38)፣ እንደ ሰውም ሕግን በመጠበቅ ፍጹም የመገዛት እና የአምልኮ ምሳሌን አሳይቷል። "ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤" (ዕብ. 5:8)። ይህ ድርብ እውነት ፣ እርሱ ራሱ አምላክ ሆኖ አምልኮ ሲቀርብለት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍጹም አምላኪ ሆኖ ሲኖር ፣ ኢየሱስን የክርስቲያናዊ አምልኮ ሁለቱንም ጫፎች የያዘ ብቸኛ ምሳሌ ያደርገዋል፤ የምናመልከው እርሱ ራሱን ነው፣ የምናመልክበትም መንገድ የተማርነው ከእርሱ ነው።

በምድረ በዳ የተደረገው የሥልጣን ፍልሚያ

ኢየሱስ በምድረ በዳ ሲፈተን (ማቴዎስ 4:8-10)፣ ዲያብሎስ የዓለምን መንግሥታትና ክብራቸውን ሁሉ አሳይቶ "ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ" አለው። የሰይጣን የመጨረሻ ግብ የአምልኮ ዒላማ መሆን ነበር። ኢየሱስ ግን "ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና" በማለት ሰይጣንን አሸነፈው። አምልኮ ማንን እንደምናገለግል የምንወስንበት የሕይወት ፍልሚያ ነው። ልብ ልንል የሚገባው፣ ሦስቱም ፈተናዎች ፣ እንጀራ፣ ዝና፣ ሥልጣን በመጨረሻ ወደ አንድ ጥያቄ ያመራሉ፦ "ለማን ትሰግዳለህ?" ስለዚህ ኢየሱስ ለዚህ ፈተና የሰጠው መልስ ሁሉ ከቃሉ ነው፤ ይህም እውነተኛ አምልኮ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የቆመ መሆኑን ያስተምረናል።

ከሳምራዊቲቱ ሴት ጋር የተደረገ ውይይት

በዮሐንስ 4 ላይ ኢየሱስ ከሳምራዊቲቱ ሴት ጋር በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተገናኘ። ሴቲቱ "አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ግን... በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ" ብላ የቦታ ክርክር አነሳች። ኢየሱስ ግን "እውነተኛ ሰጋጆች ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል" ብሎ መለሰላት። አምልኮን ከሕንፃ፣ ከተራራ፣ ከጂኦግራፊ ነጻ አውጥቶ በእውነት ላይ የተመሠረተ የልብ ስፍራ አደረገው። ይህ ውይይት የተካሄደው ከቤተ መቅደሱ ርቆ፣ ከሃይማኖታዊ ተቋም ውጭ፣ ከኅብረተሰብ ውጭ ከተገለለች ኃጢአተኛ ሴት ጋር መሆኑ ራሱ ትልቅ ትምህርት ነው፦ አምልኮ ለተከበሩና ለንጹሓን ብቻ ሳይሆን፣ ልቧ ለተጠማች ለማንኛዋም ነፍስ ክፍት ነው።

በጌቴሴማኒ የቀረበ የመገዛት አምልኮ

የአምልኮ ጥልቅ ፈተና የመጣው በጌቴሴማኒ ነው። ኢየሱስ "ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች" ብሎ በደም ላብ እየጸለየ "አባት ሆይ፥ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ" (ሉቃ 22:42) አለ። ይህ የመጨረሻው የአምልኮ ፈተና ነው ። ስሜታችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር በሚጋጭበት ቅጽበት እንኳ "የአንተ ፈቃድ ይሁን" ማለት እውነተኛ አምልኮ ነው። እውነተኛ አምልኮ የስሜት መቅረት ማለት አይደለም፤ ኢየሱስ ራሱ ጭንቀትና ሐዘን ተሰምቶት ነበር። አምልኮ ማለት ግን ያንን ስሜት ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ነው።

የግል አምልኮ እና ጸሎት

ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ከህዝብ ርቆ በብቸኝነት በጸሎት ጊዜ ያሳልፍ ነበር (ሉቃስ 5:16)።

  • ማር. 1:35 – "ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ።"
  • ሉቃስ 6:12 – አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን ሙሉ በጸሎት አሳልፏል።

ይህ የሚያሳየው የግል አምልኮ የኢየሱስን አገልግሎት እንዳጸና ነው። ትልቁ ሥራ ከመስራቱ በፊት፣ ትልቁ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት፣ ኢየሱስ መጀመሪያ ወደ አብ ፊት ተመለሰ። ይህ ስርዓት ለእያንዳንዱ አማኝ ግልጽ ምሳሌ ነው፤ ውጤታማነት ከመንፈሳዊ ጥልቀት ይቀድማል ሳይሆን ይከተላል።

በህዝብ ፊት ምስጋና

  • ማቴ. 11:25 – "አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤"
  • ዮሐ. 11:41 – አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት፣ "አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።" ብሏል።

ኢየሱስ ከተአምራት በፊት ምስጋናን በመግለጽ፣ ምስጋናን ከተአምራት ያስቀድማል። ውጤቱን ከማየቱ በፊት ያመሰግናል፤ ይህም እምነት የተሞላበት ምስጋና ውጤትን በመጠባበቅ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል።

የአምልኮና የምስጋና ኃይል

መጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ጠላትን እንደሚያሸንፍ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን ይዟል። ምስጋና ተገብሮ ወይም ሰነፍ አይደለም። እሱ ንቁ የሆነ መንፈሳዊ የመቋቋም ተግባር ነው። አምልኮ ውጊያውን ከተፈጥሮአዊው ወደ መንፈሳዊ ይለውጠዋል። ራእይ 12፥11 ላይ ወንድሞቻችን "በበጉ ደምና በምስክራቸው ቃል" አሸነፉት ይላል፤ ምስጋና እውነት የሆነውን የክርስቶስን ድል ወደ ድምፅ በመቀየር፣ ተከሳሽ ሰይጣንን ዝም ያሰኝበታል።

ንድፍ ፬፡ ምስጋና በውጊያ ውስጥ — ሦስት ታሪኮች

ግዙፍ ቅጥር ኢያሪኮ (ኢያሱ 6) ውዳሴ/ጩኸት መለከትና ታላቅ ጩኸት ውጤት ቅጥሩ ፈረሰ ብዙ ጠላት ሠራዊት ኢዮሳፍጥ (2ዜና 20) ዘማሪዎች ቀደሙ "ምሕረቱ ለዘላለም ነው" ውጤት ጠላት ራሱን አጠፋ ጨለማ ወህኒ ቤት ጳውሎስና ሲላስ (ሐዋ 16) በእስር ውስጥ ዝማሬ በመንፈቀ ሌሊት ውጤት እስራት ተፈታ

የኢያሪኮ ቅጥር መፍረስ (ኢያሱ 6)

"ሕዝቡም ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ የከተማይቱም ቅጥር ፈረሰ"

እግዚአብሔር ያዘዛቸው ጦር እንዲያነሱ ሳይሆን፣ ካህናቱ መለከት እየነፉ ታቦቱን እንዲሸከሙና በሰባተኛው ቀን ታላቅ የምስጋናና የድል ጩኸት እንዲያሰሙ ነበር። ምስጋና በመንገዳችን ያሉትን መንፈሳዊ ግንቦች የማፍረስ ኃይል አለው። ስድስት ቀናት ዝምታ፣ በሰባተኛው ቀን ግን ድምፅ — ይህ ትዕግስት የተሞላበት ታዛዥነት፣ በእግዚአብሔር ጊዜ የቀረበ ምስጋና ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያስተምረናል።

የኢዮሳፍጥ ታሪክ (2ኛ ዜና 20)

"እልልታና ምስጋናም በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር... አመጣባቸው፥ ተመቱም።"

የይሁዳ መንግሥት በሞዓብና አሞን ታላቅ ሠራዊት ሲከበብ፣ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ጦረኞችን ከማሰለፍ ይልቅ የምስጋና ቡድኑን ከሠራዊቱ ቀድሞ ላከ። አምልኮ እግዚአብሔርን ወደ ውጊያችን ያመጣዋል። ከዚህ ታሪክ በፊት ኢዮሳፍጥ ራሱ "ምን እናደርግ እንደሆነ አናውቅም፤ ዓይኖቻችን ግን ወደ አንተ ናቸው" (2ዜና 20፥12) ብሎ የጸለየው ጸሎት፣ የምስጋና ሠራዊት ወደ ግንባር ከመላኩ በፊት የነበረውን ትህትና ያሳያል። ምስጋና ከድክመት ማመን ይነሳል፣ ከግርማ ማሳየት አይደለም።

ጳውሎስና ሲላስ (ሐዋ. 16:25-26)

"በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር... የእያንዳንዱም እስራት ተፈታ።"

ተደብድበውና እግራቸው በግንድ ታስሮ ጨለማ ወኅኒ ቤት ተጣሉ። ሆኖም በመንፈቀ ሌሊት፣ በሕመም ውስጥ ሆነው መዘመር ጀመሩ! የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፣ በሮች ተከፈቱ፣ የሁሉም እስራት ተፈታ። ሌሎች እስረኞችም ይሰሙ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ምስጋና ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የነጻነት በር ከፈተ።

ማሳሰቢያ፡ ምስጋና ውጤትን ለማግኘት ብቻ አይደለም

እነዚህ ታሪኮች ምስጋና እንደ "ውጤት ማምጫ ቀመር" ተደርጎ እንዳይወሰድ ልብ ማለት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ውጤት ሳይታይ የሚቀርብ ምስጋናን ያስተምራል፦

"በለስም ባታፈራ... እርሻዎችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረታቸው ቢጠፉ... እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፥ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።"

ዕንባቆም 3፥17-18

ኢዮብ ንብረቱንና ልጆቹን ባጣ ጊዜ እንኳ "እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን" (ኢዮ 1:21) ብሎ ወደቀ ሰገደ። እውነተኛ አምልኮ ከበረከት ባሻገር፣ ራሱ እግዚአብሔርን ለራሱ ማንነት የሚያከብር ነው። ብዙ ጊዜ በጨለማ ውስጥ የሚቀርብ ምስጋና፣ ብርሃን በሞላበት ጊዜ ከሚቀርበው ይልቅ ዋጋው በእግዚአብሔር ፊት የላቀ ነው፤ ምክንያቱም የልብን እውነተኛ ታማኝነት ያሳያልና።

በዛሬው ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት

የቤተክርስቲያን አምልኮ

የጥንቷ ቤተክርስቲያን አብነት (ሐዋርያት ሥራ 2:42-47)፦ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን፣ ቤተክርስቲያን የተወለደችው በአምልኮ እሳት ውስጥ ነው። "በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ... እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ" ይላል ቃሉ። ይህ ጥምረት ፣ ትምህርት፣ ኅብረት፣ እንጀራ መቍረስ፣ ጸሎት፣ ምስጋና የጤናማ የቤተ ክርስቲያን አምልኮ አምስት ምሰሶዎች ናቸው፤ አንዱ ከጎደለ ቀሪው ይዛባል።

የተሃድሶ ዘመን የምስጋና አብዮት፦ በመካከለኛው ዘመን፣ አምልኮ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካህናት ብቻ በላቲን ቋንቋ የሚዘምሩት የኳየር ሥርዓት ሆኖ ነበር። ማርቲን ሉተር ግን "ዲያብሎስ ሙዚቃን ይጠላል" በማለት፣ መዝሙሮችን ወደ ሕዝቡ ቋንቋ (ጀርመንኛ) ተረጎመ። እንደ ቻርልስ ዌስሊና አይዛክ ዋትስ ያሉ ጸሐፍትም "የምእመናን የጋራ ዝማሬን" ወደ ቤተክርስቲያን መለሱት። ይህ ታሪካዊ ለውጥ የሚያስተምረን፣ አምልኮ የተመልካች ጨዋታ ሳይሆን የሁሉም ምእመናን ንብረት መሆኑን ነው ፤ "የካህናት መንግሥት" ተብለን ተጠርተናልና (1 ጴጥ 2፥9)።

የጋራ አምልኮ

የጋራ አምልኮ አማኞች አብረው እግዚአብሔርን ለማክበር የሚሰበሰቡበት ነው፤ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ።

ዕብራውያን 10:24-25 – "ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ ... መሰብሰባችንን አንተው..."

  • ዝማሬ፣ ጸሎት፣ ስብከት፣ ኅብረት፣ አንድነት

በጋራ አምልኮ ውስጥ የምንለማመደው የእምነት አንድነትን፣ በመንፈሳዊ ስጦታዎች መገንባትን፣ የክርስቶስ አካል በአንድነት ሲሰራ ማየትን ነው። ኢየሱስ "ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ" (ማቴ 18፥20) ብሎ ቃል ገብቷል፤ ስለዚህ የጋራ አምልኮ የክርስቶስን ልዩ መገኘት የምንቀበልበት ስፍራ ነው።

የግል አምልኮ

የግል አምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የግል፣ ዕለታዊ ግንኙነት ነው፤ በብቸኝነት ጊዜ የምናደርገው።

ማቴዎስ 6:6 – "አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ..."

  • የግል ንባብ፣ ብቻችንን መዘመር፣ ጸጥ ያለ ማሰላሰል፣ የመታዘዝ ተግባራት

የግል አምልኮ የጋራ አምልኮን ያነሳሳል፤ የጋራ አምልኮ ደግሞ የግል እምነትን ያጠናክራል። በሁለቱም መካከል ያለ አለመመጣጠን የመንፈሳዊ ሕይወት ድካም ምልክት ነው፤ የግል ግንኙነት የሌለው የጋራ አምልኮ ግብዝነትን ያፈራል፣ የጋራ ኅብረት የሌለው የግል አምልኮ ደግሞ ብቸኝነትንና ኩራትን ያፈራል።

ሰማያዊው አምልኮ

በክርስትና ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂውና ተስፋ ሰጪው እውነት፣ አምልኮ በዚች ምድር ላይ ተጀምሮ የሚያልቅ ጊዜያዊ ሥርዓት አለመሆኑ ነው። በዘመናት መካከል አባቶቻችን በስደት፣ በዋሻና በመከራ ውስጥ ሆነው በዕምባ ዘምረዋል፤ ሆኖም ያ የምድር ላይ ውዳሴ ገና ለሚመጣው የዘላለም ክብራችን፣ ለሰማያዊው ታላቅ አምልኮ ቅምሻ እና ልምምድ ብቻ ነበር።

"ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። ... ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል..."

ራእይ 4፥8፣ 11

"የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል... በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።"

ራእይ 5፥12-13

ይህ አስደናቂ ትንቢታዊ ክፍል የሚያሳየን፣ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት የፍጥረት ሁሉ ወኪሎች የእግዚአብሔርን ፍጹም ቅድስና ያለማቋረጥ ሲያውጁ፤ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ወኪሎች ደግሞ በዘላለም ዙፋን ፊት ወድቀው የክብር አክሊሎቻቸውን ሲጥሉ ነው። በምድር ላይ ያሉ መሪዎች ሥልጣንን ሲያከማቹ፣ በሰማይ ግን ትልቁ ክብር በዙፋኑ ፊት መንበርከክና አክሊልን አውልቆ መጣል ነው። ይህ የ"እኔነት" መቃብር፣ በእግዚአብሔር አክብሮት ላይ ብቻ ያተኮረ ዘላለማዊ አምልኮ ነው። ራእይ 7፥9-10 ላይ ደግሞ "ከሕዝብና ከወገን ሁሉ፥ ከነገድና ከቋንቋም ሁሉ" የተውጣጣ እጅግ ብዙ ሕዝብ በአንድነት "መድኃኒት ለአምላካችንና ለበጉ ነው" እያለ ሲጮህ እናያለን፤ ይህም አምልኮ በአንድ ቋንቋ ወይም ባህል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ዘላለማዊና ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ያረጋግጣል። ኢትዮጵያውያንም በዚያ ታላቅ ጉባኤ ውስጥ ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምንዘምርበት ቦታ ይኖረናል።

"ብቻውን አምላክ ለሚሆን መድኃኒታችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ ይሁን፤ አሜን።"

ይሁዳ 24-25

ስለዚህ ወዳጄ፣ ዛሬ የምታቀርበው ጸሎት፣ የምትዘምረው መዝሙር፣ በልብህ የምታደርገው ዝምተኛ አምልኮ ትንሽ አይምሰልህ። እነዚያ ሁሉ የዘላለም ውዳሴ ልምምዶች ናቸው፤ በምድር የጀመርከው ዜማ በሰማይ ፍጻሜውን ያገኛል። አምልኮህ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ፣ የዘላለም ማንነትህ መገለጫ ነውና በእምነት ቀጥል።